
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚዘጋጀው ጉልባን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው እና በታሪክ የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሰባኪ ወንጌል መምህር ምሕረተ አብ መራቸው ጉልባን ትርጓሜው መቀቀል መኾኑን ነግረውናል። በተለይም ለጥራጥሬ እህሎች (ለባቄላ፣ ለስንዴ፣ ለአጃ፣ ለአተር) መቀቀል የሚሰጥ ስያሜ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ጉልባን በብሉይ ኪዳንን ሥርዓት የተጀመረ እና ከዚያ ጀምሮ የመጣ መኾኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ከጥንት የነበረውን የበዓል አከባበር፣ አለባበስ እና አመጋገብ ይዘው መዝለቃቸውን ገልጸዋል።
በኦሪት ዘመን የእስራኤላውያን ከግብጽ ወደ ምድረ እርስት መሻገሪያ ዘመን ደርሶ ነበርና ሙሴ እና አሮን ለሕዝቡ ቶሎ ብላችሁ ትኩስ፣ ያልቦካ እና ያልሆመጠጠ ቂጣ አዘጋጁ ብለው መመሪያ ሰጥተው እንደነበር አንስተዋል ።
በዚህም በስደታቸው ድንገተኛ ምግብ መብላታቸውን አንስተዋል። አሁን ላይም በኦሪት ዘመን ለተፈጸመው መታሰቢያ አባቶቻችንን ከጥፋት ሀገር ወደ ርስትህ መለስሃቸው፤ ከስደት ሀገር ወደ ተስፋይቱ ምድር ኢየሩሳሌም አገባሀቸው ለማለት ጉልባን ይዘጋጃል ብለዋል።
በአዲስ ኪዳን ደግሞ በመከራ ነበርን አንተ ግን ደምህን አፍሰህ፣ ዋጋ ከፍለህ፣ ወደ ቀደመው ክብራችን ወደ ርእስተ መንግሥተ ሰማያት መለስከን በማለት የኦሪቱን ዘመን በማሰብ በዓሉ ይከበራል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ጉልባን የሚበላበት ምክንያትም የኦሪቱን ዘመን ፋሲካ ለማስታወስ ነው ብለዋል።
በቀደመው ጊዜ የእስራኤላውያን ምግብ ስንዴ ነው ያሉት መምህሩ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ላይ ስላመጹ በአጭር ጊዜ መሻገር እየቻሉ ጉዟቸው ብዙ ነበር፤ በጉዟቸውም በችኮላ የሚደርስ ምግብ እያዘጋጁ ይመገባሉ፤ ስንዴንም ስለተጠቀሙ ለጉልባን በዓል ይቀቀላል። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ባቄላ ጨምረውበት በዓሉ ይከበራል ብለዋል።
የባቄላ እና ስንዴ መቀላቀል አንድ መኾንን፣ መዋሐድን እና መተባበርን ማሳያ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ባቄላ እና ስንዴ ተቀላቅለው የሚቀቀሉት እና የሚበሉት ባሪያ እና ጌታ፣ የተማረ እና ያልተማረ፣ የሚባል አለመኖሩን ሁሉም በክርስቶስ አንድ እንደኾነ ለማስረዳት የሚፈጸም ነው ብለዋል።
አንድ መኾን እና አለመለያየትን ከሚያመላክተው ሃይማኖታዊ ትውፊት ኢትዮጵያውያን መተባበርን፣ አንድነትን፣ መከባበርን ሊማሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አንተ እንዲህ ነህ የሚል እሳቤን መተው እንደሚገባ ትውፊቱ ያስተምረናል ብለዋል።
ሰው ጎራ ከፍሎ አንዱ ሌላውን ማጥቃት ለሰው ልጅም ኾነ ለሀገር አይጠቅምም፤ መለያየት ትውልድ እና ሀገርን ይጎዳል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን ከዚህ በመማርም አንድ ኾነው ሀገርን ሌሎች ሀገራት ከደረሱበት ዕድገት እንድትደርስ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
