
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሙነ ሕማማት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል ያሳለፈው መከራ የሚታሰብባት ቅዱስ ሳምንት ናት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሰባኪ ወንጌል መምህር ምሕረተ አብ መራቸው በሰሙነ ሕማማት የክርስቶስ ሕማም እና መከራ ይታሰባል ነው ያሉት።
በሰሙነ ሕማማት በሌሎች ጊዜያት የሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ ሥርዓት አይፈጽሙም። በሰሙነ ሕማማት
ከጸሎተ ሐሙስ ውጭ ቅዳሴ አይቀደስም፤ ማሕሌት አይቆምም፤ መስቀል አይሳለምም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፤ ክርስት እና አይነሳም ነው ያሉት።
እነዚህ ሥርዓቶች በሆሳዕና ዕለት አስቀድመው የሚከናወኑ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
በሰሙነ ሕማማት ደስታ እና ተድላ ማድረግ አይቻልም፤ ምዕመናን ስጋዊ ነገሮችን ትተው የክርስቶሰን ስቃይ እና መከራውን በማሰብ ያሳልፋሉ ነው ያሉት።
ለእኔ ስትል ተንገላታህ ለማለት፤ መከራን፣ ሞትን ለማሰብ እና በረከትን ለማግኘትም ምዕመናን በባዶ እግራቸው ይሄዳሉ ብለዋል።
የሰሙነ ሕመማት ቀኖች የራሳቸው ስያሜ እና አስተምህሮ እንዳላቸው ተናግረዋል። ቤተክርስቲያን የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመከወን እንደምታሳልፍ ገልጸዋል። ከሰሙነ ሕማማት ቀናት መካከል ዕለተ ሐሙስ ሕጽበተ እግር ትባላላች። በዚህች ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ አጥቧል ነው ያሉት። ይህም የሚያሳየው የዓለምን ኃጥያት ለማጠብ የመጣ መኾኑን ነው።
ለኃጥያት እና ለዲያቢሎስ ባርነት መኖር ማብቃቱ፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ዕለት ነው ያሉት መምህሩ ራሱ ዝቅ ብሎ አክብሮትን ያስተማረበት መኾኑንም ተናግረዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርትን እግር በማጠብ አርዓያ ኾኖ የታየበት ቀን መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
