በአማራ ክልል 38 የመሶብ ማዕከላትን ለመገንባት እየተሠራ ነው።

15

 

ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እና የኢትዮ ኮደርስ አፈጻጸምን እየገመገሙ ነው።

የአማራ ክልል ሲቪል ሠርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረ ማርያም የባሕርዳር እና የደሴ ከተሞች የሞሰብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በ45 ቀናት ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አስታውሰዋል። ማዕከላቱ በፍጥነት እና በቅልጥፍና መሥራት እንደሚቻል ያስተማሩ ናቸው ብለዋል።

የአሠራር ሕጎችን በማሳወቅ ተቋማት እና አገልግሎትን በመለየት ወደ ሥራ ተገብቷል። ሠራተኞችን በማሠልጠን እና ለቴክኖሎጅ ቅርብ የኾኑ ወጣቶችን በመለየት ወደ ማዕከሉ ማስገባታቸውን አንስተዋል።

በክልሉ በሦሥት ዙር የመሶብ ማዕከላትን በመገንባት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል። በ25 መካከለኛ ከተማ አሥተዳደሮች የመሶብ አገልግሎትን ለማስጀመር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት 38 ማዕከላትን አስገንብቶ ለማስመረቅም እየተሠራ እንደኾነ ጠቁመዋል። ከ72 ሺህ በላይ አገልግሎቶች በሦሥት ማዕከላት እየተሰጡ መኾናቸውን አንስተዋል።

ትምህርት፣ ጤና፣ ባሕል እና ቱሪዝም፣ የመሬት ዘርፍ አገልግሎቶች እና ሌሎች ተቋማትም ወደ መሶብ አንድ ማዕከል ለማስገባት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመስቀሉ የሚያስተምረን የጥል ግድግዳን አፍርሰን ለእርቅ መቆምን ነው።
Next articleጸሎተ ሐሙስ የትህትና ቀን