መስቀሉ የሚያስተምረን የጥል ግድግዳን አፍርሰን ለእርቅ መቆምን ነው።

6

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የስቅለት በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ የቦርድ ሠብሣቢ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መላዕከ ብርሃን ፍሰሐ ጥላሁን ናቸው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው መከራ የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የታረቀበት እና በጥል ግድግዳ ተራርቀው የነበሩ ወገኖች የተገናኙበት ነው ብለዋል። ታላቅ የዕርቅ እና የሰላም ድልድይ መኾኑንም ተናግረዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለው መለኮታዊ ዋጋ በመካከላችን የቆሙትን የክፋት እና የቂም ግንቦችን በማፍረስ እንደኾነ ነው የገለጹት። በምትኩ በይቅርታ እና በወንድማማችነት የተገነባ አዲስ ማንነትን ሰጥቶናል ነው ያሉት።

የመስቀሉ ቃል የሚያስተምረን እንደ ክርስቶስ የጥልን ግድግዳ አፍርሰን ለዕርቅ እና ለሰላም እንድንቆም ነው ብለዋል።

ዛሬ ለሀገራችን እና ለወገናችን ከምንም በላይ በመስቀል ላይ የተመሠረተው ይህ የሰላም እና የፍቅር መንገድ ያስፈልጋል ብለዋል።

መስቀል ራስን ዝቅ አድርጎ ለሌላው መሰዋትን፤ ጥላቻን በትዕግሥት ማሸነፍን እና ይቅርታን የሚያስተምር እንደኾነ ነው የገለጹት።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ኾኖ መከራ ለሚያጸኑበት “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው” እንዳለ ይህ የይቅርታ ጥሪ ዛሬም በመካከላችን ላለው ቅሬታ እና ልዩነት ብቸኛው ፈውስ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

እንደ ሀገር እና እንደ ክልል የገጠሙንን የልዩነት እና የጥል ደመናዎችን ሕዝቡ በመስቀሉ የሰላም ብርሃን እንዲገፍም በመግለጫው ጥሪ ተላልፏል።

በዓሉ የክርስቶስን ፈለግ ተከትለን ለሰላም የምንቆምበት፤ ለወንድም እና እህቶቻችን የምንራራበት እና ለእርቅ የምንዘጋጅበት ሊኾን እንደሚገባም በመግለጫው ተነስቷል።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም አማራጭን ባልተቀበሉ የጽንፈኛ ቡድን አባላት ላይ እርምጃ ተወሰደ።
Next articleበአማራ ክልል 38 የመሶብ ማዕከላትን ለመገንባት እየተሠራ ነው።