ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው በምዕራብ ጎጃም ዞን እና በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የጽንፈኛው ቡድን አባላት ላይ ርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
የምሥራቅ ዕዝ አንድ ኮር ከመጋቢት 21/2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም ባከናወነው የተቀናጀ ኦፕሬሽን 23 የቡድኑ አባላት ርምጃ ተወስዶባቸዋል። በተጨማሪም 8ቱ ተማርከዋል፤ 6ቱ እጃቸውን ሰጥተዋል፤ 7ቱ ደግሞ በሰላም አማራጭ ወደ መንግሥት መመለሳቸው ተገልጿል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል መኳንት ገበየሁ የተባለ የጽንፈኛ ቡድኑ የሻለቃ መሪ፣ አድጎ ጎሹ አንዷለም የተባለ የሎጀስቲክስ ኀላፊ እና ኤልያስ አየለ የተባለ የመቶ አለቃ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።
በኦፕሬሽኑ ወቅት የሰው ኃይሉ ከመበተኑ ባለፈ በርካታ የጦር መሣሪያዎች እና ቁሳቁሶች ተማርከዋል።
ከእነዚህም መካከል 18 የኤኬኤም (ክላሽንኮቭ) መሣሪያዎች፤ 5 የቃታ መሣሪያዎች፤1 የፖሊስ ሬዲዮ መገናኛ፤ በርካታ ተተኳሾች፣ ወታደራዊ ትጥቆች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።
በጎጃም ቀጣና ግዳጃቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ የኮሩ መሪዎች እና አባላት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቿ በተለያየ ጊዜ የሰነዘሩባትን የጥፋት ሴራ በጀግንነት ስታከሽፍ የኖረች ሀገር መኾኗን አስታውሰዋል።
አሁንም የውጭ ኀይሎችን ፍላጎት በማንገብ ሀገር ለማፍረስ እና ሕዝብን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን፣ መከላከያ ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጋር በመኾን በጽናት እየመከተ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ጽንፈኞችን ከየተወሸቁበት የመልቀም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል። መረጃው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
