
ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም(አሚኮ) ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የሰውን ሰጋ ለብሶ በምድር ተገልጧል። በሰሞነ ሕማማትም መከራን ተቀብሏል፤ ምስጢራትን ገልጧል።እለተ ሐሙስ ድግሞ የምስጢራት ቁልፍ ናት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጎንደር አዘዞ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር ምክሩ ተረፈ በዕለተ ሐሙስ ሦሥት ምስጢራትን ክርስቶስ መፈጸሙን ተናግረዋል።
የሐዋርያትን እግር በማጠብ፤ ምስጢረ ቁርባንን በመግለጥ፤ በጌቴ ሴማኒ ሥርዓተ ስግደት እና የጸሎት ሥነ ሥርዓትን በማስተማር ምስጢራትን መፈጸሙን ገልጸዋል።
አምላክ ኾኖ ሳለ የሐዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ ማጠቡ ትህትና እና ትዕግስትን ለዓለም ለማስተማር ነው ብለዋል። ትህትና እና አገልጋይነትን ከክርስቶስ በመማር በቅንነት በማገልገል በትህትና መፈጸም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለሐዋርያት “ይህ ስለ እናንተ የሚቆረሰው ስጋየ ነው፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስሰው ደሜ ነው” በማለት ምስጢረ ቁርባንን ሲገልጥ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳን ማካተቱንም አንስተዋል። ይሁዳ አሳልፎ የሚሰጠው ጠላት ቢኾንም አብሮ ማሳተፉ ጠላትን መውደድ እንደሚገባ ለማሳየት መኾኑንም ገልጸዋል።
በጌቴ ሴማኔ የጸሎት እና የስግደት ሥርዓትን ማስተማሩ ደግሞ በፈተና እና በመከራ ጊዜ መጸለይ እንደሚገባ ለማሳየት ነው ብለዋል።
መከባበር እና ትህትናን በሕይወት ውስጥ በመግለጥ ፍቅር እና አንድነትን ማስቀደም እንደሚገባም ተናግረዋል። ዕለቱ ጸሎተ ሐሙስ፤ ሕፅበተ ሐሙስ፤ የምስጢር ቀን ተብሎ እንደሚጠራም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
