“ዓለምን በሕመሙ ፈወሳት፤ እየወጋችው ወደዳት”

9
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ የከፈለው መስዋዕትነት የሚታሰብበት ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይሰኛል። በዚህ ሳምንት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጅ የከፈለው መስዋዕትነት፣ የተቀበለው መከራ ይታሰባል። ስለ ፍቅሩ፣ ስለ ርህራሄው፣ ስለ ቸርነቱ እና ስለ ምህረቱ ምስጋና ይቀረብበታል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የአራቱ ጉባኤያት መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ ሰሙነ ሕማማት የተቀደሰች እና ልዩ ሳምንታችን ናት፤ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የመጨረሻ ስጦታ ያለውን ስጦታ የሰጠባት ሳምንት ናት ይላሉ።
ስሙነ ሕማማት የመጨረሻው የፍቅር ዋጋም የተገለጠባት ናት፤ እግዚአብሔር ይህንን ዓለም እንዲሁ ወድዶታልና እንደተባለ። ስጦታ የፍቅር መገለጫ ነው፤ የሰው ልጅ ከልቡ የሚወደውን ሰው ለልቡ መገለጫ የሚኾን ስጦታ ይሰጣል፤ ለጠላቶቹ ግን አይሰጥም።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ጠላቶቹ ኾነን ሳለን ወደደን፤ የመጨረሻውን ስጦታ ሰጠን፤ ይቅር አለን ታረቀን፤ ራሱን ሰጥቶ ፍቅሩን አሳየን፤ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ ራስን ከመስጠት የበለጠ ፍቅር የለምና።
አባት ልጁን ቢወደው እንጀራ ቆርሶ ያጎርሰዋል፤ ከልብሱ ቀድዶ ያለብሰዋል፤ እርስቱን ያወርሰዋል፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱን ሰጠ፤ ታመመ፤ ደማ፤ የማይደፈረው ተደፈረ ይላሉ ሊቁ።
በደሙ ዓለምን ያነጻ፣ የተቀደሰ ፊቱ ላይ እርኩስ ምራቅ ተተፍቶበታል፤ እውቀትን የገለጠ እርሱ እንደማያውቅ ፊቱን ሸፍነው ክርስቶስ ማነው? በጥፊ የመታህን ተናገር እያሉ በጥፊ መትተውታል፤ የወደቁትን የሚያነሳቸውን፤ የጎበጡትን የሚያቀናቸውን እርሱን እርጥብ መስቀል አሸክመው ተጎንብሶ እንዲሄድ አድርገውታል።
ሕሙማንን የሚፈውሱትን እጆቹን የፍጥኝ አሥረው ጎትተውታል። እርሱ ይሄን ሁሉ መከራ የተቀበለው ለሰው ልጅ ፍቅር ሲል ነው። እንዲህ አይነት ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው ? እንዲህ አይነት ቸርነትስ እንደምን ያለ ቸርነት ነው ?
ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሰጠው ስጦታ ምንድን ነው ብንባል ራሱን ነው የሰጠው እንላለን ይላሉ። ትልቁ ስጦታችን ክርስቶስ ነው፤ ለራሳችን ዘውድ፤ ለእግራችን የሚኾን መሠረት፤ ለሰውነታችን ልብስ፤ ለዓይናችን ብርሃን፤ ለጆሯችን በጎ ቃል እርሱ ነው ይላሉ ሊቁ።
ሰሙነ ሕማማት እግዚአብሔርን ስጦታ አድርገን የተቀበልንበት ነው፤ በሰሙነ ሕማማት ራሱን ለሰጠን ጌታ ራስን መስጠት ይገባናል፤ ለስጋ ድሎት የሚኾነውን ነገር መተው፤ ለእርሱ ፍቅር ራስን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሰሙነ ሕማማት የምንሰግደው ለእኔ ብለህ ወደቅህ ወይ? እኔ ትቢያ ልሁንህ፤ ለእኔ ብለህ ተደፋህ ወይ? እኔ ልደፋልህ፤ ለእኔ ብለህ ተገረፍክ ወይ? እኔ ልገረፍልህ እያልን ራሳችን ለጌታ ፍቅር ለማሳየት ነው፤ በሰሞነ ሕማማት የበለጠ ፍቅርን እናሳያለን እንጂ ዓመቱን ሁሉ ትተን በሰሙነ ሕማማት የክርስቶስ የምንኾን አይደለም፤ ክርስቲያን ከክርስቶስ ፍቅር ተለይቶ አይኖርም ነው ያሉት።
በሕማማት ተድላ እና ደስታ አይደረግም፤ በሕማማት የተደሰተ ሰው በትንሣኤ ሊያለቅስ ይገባዋል ተብሎ ተጽፏልና። ሰሙነ ሕማማት ከጌታ ጋር የምንታመምበት ነው፤ ከክርስቶስ ጋር የታመመ ሰው ከክርስቶስ ጋር ይነሳልና፤ የእርሱ ሕማማት ለእኛ ፈውስ እና መድኃኒት ናቸው ነው የሚሉት።
ሲታሰር ከታሰርንበት እርግማን ፈትቶናል፤ ቤዛ ኾኖናል፤ ሲከሰስ 5 ሺህ 500 ዘመን የነበረውን ክስ ደምስሶልናል፤ የአይሁድን ይሰቀል ይሰቀል ሲሰማ የአጋንንትን ማስፈራራት ለሰማንበት ጀሮ ቤዛ ኾኖልናል። ስለ ተገረፈ በሕማም እና በሞት የተገረፍነውን ግርፋት አርቆልናል፤ በመራቆቱ ከጸጋ ተገፍፈን የነበርነውን ጸጋ መልሶ እርሱ አልብሶናል፤ በመራቡ ምክንያት በቅዱስ ስጋው በክቡር ደሙ አጥግቦናል።
በመቸንከሩ ተቸንክረንበት ከነበረው የሞት ችንካር አውጥቶናል፤ የሾህ አክሊሉን በመድፋቱ በእኛ ላይ የነበረውን የሐጥያት እሾህ ነቅሎልናል፤ በመሰቀሉ ሞትን ሰቅሎታል፤ ድል ነስቶታል፤ በምድር እና በሰማይ፣ በሕዝብ እና በአሕዛብ፣ በሰውና በመላዕክት የነበረውን ጥል አፈራርሷል፤ እርቅንም ሰጥቷል ብለዋል።
ከክርስቶስ ጋር የታመመ ከክርስቶስ ጋር ያርፋል፤ በክርስቲያኖች ስቃይ ውስጥ ዘላለማዊ እረፍት አለ። እርሱ እርቃኑን ኾኖ የብርሃንን ልብስ አለበሰን፤ ጠላታችንን ዲያቢሎስን አሠረው፤ የሞትንም መውጊያ ሰበረው፤ የዕዳ ደብዳቤውንም ቀደደው ይላሉ ሊቁ።
ሕመሙ ፈውስ የኾናቸው፤ ሞቱ ሕይወትን የሰጣቸው ክርስቲያኖች ሕማሙን እያሰቡት፤ የተሰጣቸውን ፍጹም ፍቅር እያከበሩት፤ ስለ ቸርነቱ፤ ስለ ምህረቱ እና ስለ ፍቅሩ ምስጋና እያቀረቡለት ነው።
እርሱ እንዳደረገ የሚጠሏችሁን ውደዱ፤ የሚገፏችሁን ደግፉ፤ ፍቅርንም ስጡ፤ ያን ጊዜ እርሱን ትመስላላችሁ።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሠሩ ኃይሎችን የጸጥታ ኃይሉ አይታገስም” ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ
Next article“ስለ ትህትና ዝቅ አለ፤ የአገልጋዮቹን እግር አጠበ”