
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የሚሊሻ ኃይሉ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት እንደሚወጣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ የሚሊሻ ተቋሙ ሚና ሕግን እና ሥርዓትን ማስከበር ነው ብለዋል። በቀጣይ ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ሰላማዊነቱ እንዲጠበቅ በትጋት ይሠራል ነው ያሉት።
የምርጫ ቁሳቁስ በየአካባቢው እንዲደርስ፤ መራጩ ሕዝብ፣ እጩዎች እና የምርጫ አሥፈጻሚዎች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት ለመወጣት የሚሊሻ ኃይሉ በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ የሚፈልገውን መንግሥት የሚመርጠው በካርዱ ነው ያሉት ኮሚሽነር አስቻለ ሕዝቡ የመምረጥ መብቱ በየትኛውም መንገድ ሊነፈግ አይገባም ነው ያሉት።
ይህንን የሚያስተጓጉሉ አካላትን እየተከታተለ የሚሊሻ እና የጸጥታ አካሉ የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
“ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሠሩ ኃይሎችን የጸጥታ ኃይሉ አይታገስም” ነው ያሉት። ለዚህም ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት እና ከመላው ሕዝብ ጋር በመኾን በቁርጠኝነት እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት መሥራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የሚሊሻ ኃይሉ የወጣው ከሕዝብ አብራክ በመኾኑ ሕዝቡ ሊደግፈው እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
