
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሣኤ በዓል እና ነዳጅን በቁጠባ ለመጠቀም የሚሠራውን ሥራ ሰበብ በማድረግ ለበዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተለይም የእንስሳት ግብይት ላይ ከባለፈው ዓመት ጭማሪ ማሳየቱን መታዘባቸውን ጠቁመዋል።ምርቶች በቀላሉ የሚገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቀዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት እና የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማርካት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አትክልት አሳቤ ለትንሣኤ በዓል ምንም የምርት እጥረት ሳይገጥም ለማሳለፍ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ መሠራቱን ገልጸዋል። በተሠራው ሥራም ምንም አይነት የምርት አቅርቦት ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።
ለበዓሉ የሚኾኑ የቁም እንስሳት፣ የዶሮ፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ምርቶችን በበቂ መጠን ወደ ገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ከተቋማት ጋር በጋራ በመሥራት በእንስሳት ማድለብ በተሰማሩ ማኅበራት እና በአርሶ አደሮች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት ለገበያ እንዲቀርቡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶችን በብዛት እንዲያቀርቡ ተደርጓል ነው ያሉት።
የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማኅበረሰብ እንዲዳረስ እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳዳሩ ዜጎችም በተገደበ ዋጋ ምርቶችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና የዋጋ ንረትን ለመከላከል አምራቹን ከሸማቹ ጋር የሚያገናኙ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት በክልሉ ትልልቅ ከተሞች ተገንብተው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሠጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በእንስሳት እና በምርት ግብይት ላይ ዳላላን እና ሕገወጥ ነጋዴን ለመከላከል በቅንጅት ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል። በበዓል ስጦታ ይሰጣል እንጂ ዋጋ አይጨመርም ነው ያሉት።
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ለዚህ ሥራም ኅብተሰቡ መረጃ በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
