
ባሕር ዳር: መጋቢት30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከንዱ ወንዴ የፋሲካ በዓልን በሰላም ለማሳለፍ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።
#ከአታላዮች እና አጭበርባሪዎች መጠንቀቅ
በበዓል ወቅት “ሎተሪ ደርሶዎታል”፣ “በጣም ርካሽ የንግድ ዕቃዎች አሉ” በሚሉ አሳሳች መልዕክቶች ሊፈጠሩ ከሚችሉ መጭበርበሮች ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ማንኛውንም ግብይት በሕጋዊ የንግድ ተቋማት እና በታወቁ የገበያ ቦታዎች ብቻ ማከናወን ይገባልም ብለዋል።
#የሕገ ወጥ እንስሳት ግብይት እና የቤት ሥርቆት
👉የበዓል እርድን ምክንያት በማድረግ የተሠረቁ እንስሳት ወደ ገበያ ሊወጡ ስለሚችሉ ኅብረተሰቡ እንስሳትን ሲገዛ በሕጋዊ መንገድ ከተዘጋጁ የገበያ ሥፍራዎች ብቻ መኾን አለበት።
#ማኅበረሰቡ በሌሊትም ኾነ በቀን ወደ ጸሎት ወይም ወደ ገበያ በሚወጣበት ወቅት የመኖሪያ ቤቶች ለሥርቆት እንዳይጋለጡ በቂ ጥበቃ ማድረግ ይገባል።
#ከሐሰተኛ የብር ኖቶች ራስን መጠበቅ
በግብይት እንቅስቃሴ ወቅት የብር ኖቶቹን በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልጋል። ከሐሰተኛ የብር ኖት ሥርጭት ለመዳን የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን (እንደ ሞባይል ባንኪንግ፣ ቴሌብር እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን) መጠቀም እንደሚገባም መክረዋል። አጠራጣሪ ኹኔታዎች ሲገጥሙ በአቅራቢያ ለሚገኙ ባንኮች ወይም ለፖሊስ ማሳወቅ ይገባል ብለዋል።
#የትራፊክ ደኅንነት እና የትራንስፖርት ታሪፍ
👉አሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ ፍጥነትን መቀነስ፣ ሳይጠጡ ማሽከርከር እና ከጭነት አቅም በላይ አለመጫን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
👉ከሕጋዊ ታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ የትራንስፖርት ስምሪቶችን ለፖሊስ እና ለትራፊክ አካላት መጠቆም ይገባል ብለዋል።
#የእሳት አደጋ እና የሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር
በበዓል ዝግጅት ወቅት የሚፈጠሩ የኤሌክትሪክ አጠቃቀም እና የምግብ ማብሰያ እሳት አደጋ እንዳያደርሱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
#አስፈላጊ የኾኑ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን (ዘይት፣ ስኳር፣ ወዘተ) በመደበቅ እና ዋጋ በመጨመር ኅብረተሰቡን የሚያማርሩ ነጋዴዎች ላይ ፖሊስ ከንግድ ግብረ-ኃይል ጋር በመኾን ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል። ማኅበረሰቡም ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
