
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ ተቋማት የ2018 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የ25 ዓመታት አሻጋሪ እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ በመገባቱ ባለፉት ወራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። በከተማ ዘርፍ ተቋማት ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሠጠ ይገኛል ነው ያሉት።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል። አስፈላጊ መሠረተ ልማትን በማሟላትም የኢንዱስትሪን መንደሮች የማስፋፋት ሥራ እና የሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
የኮሪደር ልማት የከተሞችን ውበት እያጎላ፤ ለቱሪዝም የተሻለ ከተማን እየፈጠረ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው።
በቤት ልማት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖር ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በቀጣይ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።
ገጠር እና ከተማን የማስተሳሰር ሥራ በመሥራት ምርቶች በቀጥታ በገበያ ማዕከላት እንዲቀርቡ በማድረግ በከተማ የሚገኘውን ማኅበረሰብ የኑሮ ውድነት ጫና መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፍም የቅርስ ጥበቃ እና ጥገና መካሄዱን ገልጸዋል። በዚህም የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት መቻሉን ነው የተናገሩት።
የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል የታዩ ውስንነቶችን በቀጣይ ማስተካከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
