ሕገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል።

15

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የትራንስፖርት ችግር እንዳይኖር ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው የትራንስፖርት አቅርቦት ስምሪት ዳይሬክተር ጌታቸው መርሻ በበዓሉ ወቅት የሚኖረውን ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ በሁሉም አካባቢዎች የትራንስፖርት እጥረት እንዳይከሰት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በተለይም ዓለም አቀፍ የነዳጅ እጥረትን በምክንያትነት በመጠቀም በአገልግሎቱ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ልዩ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

ከታሪፍ ውጭ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል መናኽሪያዎች በስማርት ቲኬት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ተናግረዋል። ተጓዦች በመናኽሪያ መስኮቶች ብቻ በመቁረጥ ራሳቸውን ከብዝበዛ እንዲጠብቁም አሳስበዋል።

በሕገ-ወጥ መንገድ ትኬት በሚሸጡ አካላት ላይም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን እርምጃ እየተወሰደ ይገኛልም ብለዋል።

የበዓል ሰሞን ትራንስፖርትን የተሻለ ለማድረግ በሚሠራው ተግባር ኅብረተሰቡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ከባለሙያዎች እና ከጸጥታ አካላት ጋር እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

ቢሮው ከመነኸሪያ ውጭ ተጨማሪ ክፍያ በሚጠይቁ እና ሕገ-ወጥ ድርጊት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አሳስበዋል።

አግባብነት የሌላቸው ሕገ ወጥ ተግባራት በሚፈጸሙበትም ወቅት በነጻ የስልክ መስመር 923 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻልም ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፀሐይ ኃይል ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀው አመልድ ኢትዮጵያ
Next articleበቀጣይ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል።