በፀሐይ ኃይል ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀው አመልድ ኢትዮጵያ

8
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሶላር ኃይልን መጠቀም ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ሁነኛ መፍትሔ ነው። ለነዳጅ ግዥ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬም ያስቀራል።
ንጹሕ የኃይል ምንጭ በመኾኑ የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ ነው።
በአመልድ ኢትዮጵያ የኤሌክትሮ ሜካኒካል መሐንዲስ ወርቁ አቻምየለህ ተቋሙ ባለፉት ሦስት ዓመታት የፀሐይ ኃይልን ለቢሮ አገልግሎት፣ ለመጠጥ ውኃ እና ለመስኖ ፕሮጀክቶች በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለው ይገኛል ብለዋል።
ተቋሙ የሚጠቀመው ኃይል ሙሉ በሙሉ ከፀሕይ በሚያመነጨው ኃይል ነው። በዚህም ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና ከነዳጅ ጥገኝነት ነጻ ወጥቷል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በዋናው ቢሮ ከፀሐይ ብርሃን 30 ኪሎ ዋት ኃይል በማመንጨት ያልተቆራረጠ ኃይል ይጠቀማል፤ አመልድ ሁሌም መብራት አለ፤ ለጀነሬተር ነዳጅም አይገዛም ነው ያሉት።
ከቢሮው በተጨማሪም በተመረጡ የክልሉ አካባቢዎች ተመሳሳይ የፀሐይ ኃይል በማመንጨት እየተጠቀመ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። በክልሉ በሚገኙ ከ20 በላይ ታላላቅ የውኃ ፓምፖች ላይም ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑን አብራርተዋል።
የሶላር ኃይል በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት እጅግ አዋጭ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ሌሎች የመንግሥት እና የግል ተቋማትም ይህንን የኃይል አማራጭ ቢጠቀሙ ከኤሌክትሪክ ወጭ እና ከነዳጅ ጥገኝነት ከመዳናቸው ባለፈ ያልተቆራረጠ ኃይል ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ባለሙያው መክረዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርእሰ መሥተዳድር ሹመትን አራዘሙ።
Next articleሕገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል።