” ፖሊሶቻችን ሀገር እና ሕዝብ የሰጧቸውን አደራ መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ የሚጠብቁ መኾን ይገባቸዋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

10
ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች መክፈቻ ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ፖሊስ በሚሰጠው አገልግሎት ታማኝም አሳማኝም መኾን አለበት ብሎ ያምናል ብለዋል።
ዛሬ “ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በሚካሄደው 20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች መክፈቻ ጉባኤ ላይ መገኘታቸውን ገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር ) መሪነት የተጀመረው የፖሊስ ሪፎርም፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኃይልን ዘመኑን የዋጀ፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀት የዳበረ እና ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መኾን የቻለ ተቋም እንዲኾን አስችሎታል ብለዋል።
ፖሊሶቻችን ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡ እና ለህሊናቸው ታማኝ መኾን ይጠበቅባቸዋል። “አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ” ብለው የሚያምኑ እና ሀገር እና ሕዝብ የሰጧቸውን አደራ መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ የሚጠብቁ መኾን ይገባቸዋል።
የፖሊስ ኃይላችን የጥፋት ኃይሎች በሀገራችን እና በሕዝባችን ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት በአንድነት በመቆምና መስዋዕትነት በመክፈል ቀልብሷል፤ ይህም ለሁላችንም ኩራት ነው ብለዋል።
በቀጣይም የሀገርን እድገት የማይፈልጉ ኃይሎችን ሴራ በንቃት የማክሸፍና በመጭው ግንቦት የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስ ኃይላችን የላቀ ኃላፊነት አለበት፡፡ መዲናችን ለምታስተናግዳቸው ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ስኬትም የተለመደ ታሪካዊ ሚናውን ሊወጣ ይገባል።
የፖሊስ መሪዎች እና የሠራዊቱ አባላት በዕውቀት፣ በታማኝነትና በሕዝብ አገልጋይነት ስነ ልቦና ለላቀ ተልዕኮ እንድታዘጋጁ አደራ እላለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በአምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።