
ባሕር ዳር: መጋቢት29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) #በአማራ ክልል የበልግ ወቅትን ተከትሎ ሊከሠቱ የሚችሉ 10 የጤና ሥጋቶች መለየታቸውን ከክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘ መረጃ እማኝ ነው።
#ዋና ዋናዎቹም ወባ እና ኮሌራ ናቸው። ኩፍኝ፣ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ፣ እከክ እና በጎረቤት ሀገራት የታየው የማርበርግ ቫይረስም ሌሎች ስጋቶች ናቸው።
ኢንስቲትዩቱ ሥጋቶችን የለየው ያለፉ ዓመታትን የበሽታዎችን ሥርጭት መረጃዎች መሠረት በማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ባስቀመጠው መለኪያን መሠረት መኾኑን የኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት አሥተባባሪ አበበ ሲሳይ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመኸር ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ሥጋቶችን እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መኾኑን አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት አሥተባባሪ አበበ ሲሳይ ኢንስቲትዩቱ በ36 በሽታዎች ላይ ቀጣይነት ያለው ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 22ቱ ወዲያውኑ ሪፖርት የሚደረጉ ናቸው። 14ቱ ደግሞ በየሳምንቱ ሪፖርት እየተደረገባቸው ክትትል የሚደረግባቸው ናቸው።
እንደሥተባባሪው ገለጻ የበሽታዎችን ሥርጭት በቅርበት ለመከታተልም ጠንካራ የቅኝት (Surveillance) ሥርዓት ተዘርግቷል። ማንኛውም የጤና አደጋ ቢከሰት ፈጣን እርምጃ መውሰድ የሚያስችል “የአደጋ ጊዜ ምላሽ ቅድመ ዝግጅት ዕቅድ” ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ችግሮች ሲከሰቱም ከአንድ ማዕከል ኾኖ ለመምራት የአደጋ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚቋቋም ይኾናል ብለዋል ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
