ባሕር ዳር፡ መጋቢት 28/2018 (አሚኮ) ወይዘሮ ባንቹ ታረቀኝ ከ10 ዓመት በፊት የልብ የደም ባልብ መጥበብ ገጥሟቸው ነበር። ሕመሙን ሳያውቁት ለረጅም ጊዜ ቆይቶባቸው እንደነበርም ነግረውናል።
በወቅቱ በተደጋጋሚ የቶንሲል ሕመም ሲገጥማቸው ይኖሩበት በነበረ አካባቢ የሕክምና ማዕከል ባለመኖሩ እና ሕመሙ ባለመታከሙ ለልብ ሕመም መጋለጣቸውን ገልጸዋል። ይህንንም ለሌላ ሕክምና በሄዱበት አጋጣሚ ማወቃቸውን ነው የተናገሩት።
በአቅራቢያቸው የልብ ባልብ የሚቀይር የሕክምና ማዕከል ባለመኖሩ ቶሎ መታከም አልቻሉም ነበር። በኋላ ግን በቀድሞ ተማሪያቸው የእገዛ ጥየቃ መሠረት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው በሚታከሙበት ሕክምና ማዕከል ከፊል ወጭ ተሸፍኖላቸው አንዱ የልብ ባልብ ተቀይሮላቸዋል። አሁን ላይ በጥሩ ኹኔታ ላይ እንዳሉም ነገረውናል።

በአፊላስ ጠቅላላ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ልዑል ሰሎሞን ሪዩማቲክ የልብ ሕመም (የልብ ባልብ ጉዳት) በልብ ውስጥ ደምን ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ለማሳለፍ የሚረዱ የልብ በሮች (ባልቦችን) የሚያጠቃ መኾኑን ተናግረዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሕመሙ የሚጀምረው ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 15 ዓመት ያሉ ታዳጊዎች ላይ እንደኾነም ገልጸውልናል።

ለሪዩማቲክ የልብ ሕመም ከሚያጋልጡ መንስኤዎች ውስጥ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ፤ በሰው የተጨናነቀ ቤት ውስጥ መኖር፤ ተደጋጋሚ የጉሮሮ ሕመም እና የቶንሲል መቆጣት እንደኾኑ ገልጸውልናል።

ከሪዩማቲክ የልብ ሕመም ምልክቶች፦

ትኩሳት

ተደጋጋሚ የጉሮሮ ሕመም

የመገጣጠሚያዎች በተለይ የጉልበት እና የቁርጭምጭሚት ሕመም

ቀያይ የቆዳ ላይ ሽፍሽፍታዎች በተለይ በደረት፣ ሆድ እና ጀርባ ላይ

በመገጣጠሚያዎች አከባቢ የሚወጡ እብጠቶች

በቀላል እንቅስቃሴ የድካም ስሜት መሰማት

የትንፋሽ ማጠር ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።

ለሪዩማቲክ የልብ ሕመም የሚደረጉ ምርመራዎች፦

በጤና ባለሙያዎች የልብ ማዳመጫ የሚደረግ ምርመራ፤

የአልትራሳውንድ ሞገዶችን በመጠቀም ልብ ያለበትን ይዘት በቀጥታ የሚያሳይ ምርመራ፤

የደረት ኤክስሬይ ምርመራ እና
የደም ምርመራዎች እንደሚደረጉ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶክተር ልዑል ሰሎሞን ጠቅሰዋል።

ለሪዩማቲክ የልብ ሕመም የሚደረጉ ሕክምናዎች፦

በሽታው በሪዩማቲክ ፊቨር ደረጃ እንዳለ ቅድሚያ በጸረ ባክቴሪያ መድኃኒት ማከም

በሽታው ተባብሶ የልብ ድካም ካመጣ የልብን ሥራ የሚያግዙ መድኃኒቶችን መስጠት

የልብ ባልቦች በከፍተኛ መጠን ከተጎዱ በሰው ሠራሽ ባልቦች የሚተኩበት የቀዶ ጥገና ሕክምና እንደሚከናወን ስፔሻሊስቱ ተናግረዋል።

የሪዩማቲክ የልብ ሕመም መከላከያ መንገዶች፦

አስቀድሞ ተጋላጭነትን መቀነስ

የጉሮሮ ሕመም እና የቶንሲል መቆጣትን ሳያቆዩ በጸረ ባክቴሪያ መታከም

በየወሩ የሚሰጠውን የሪዩማቲክ ፊቨር ድግግሞሽ መከላከያ መርፌ በአግባቡ በመወጋት መከላከል ይገባል ነው ያሉት።