“የተጠናከር የሕግ የማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው” ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)

4

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ እና በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ለፖሊስ አባላት ሥልጠና እየሰጠ ነው።

የሥልጠናው ተሳታፊ የፖሊስ አባላት የምርጫ ቁሳቁስን፤ የምርጫ ጣቢያን እና የመራጮችን ደኅንነት ለመጠበቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሰላማዊ ምርጫ እንዲከናወን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) በክልሉ የእገታ ወንጀል ተስፋፍቶ እንደነበር አስታውሰዋል። የፖሊስ መዋቅርን ሪፎርም በማድረግ እና በትኩረት በመሠራቱ የእገታ ወንጀል እንዲቀንስ መደረጉን ተናግረዋል።

በ2018 ዓ.ም የተቀናጀ ሥራ በማከናወን በክልሉ የእገታ ወንጀል መቀነሱን ነው የገለጹት። ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም አንስተዋል።
ጽንፈኛ ታጣቂ ኃይሎች ንጹሐንን እየገደሉ እና ውድመት እያደረሱ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ጋር የሚሠሩ ጽንፈኛ ኃይሎችን አደብ ለማስገዛት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር ሕግ የማስከበር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

በርካታ የታጣቂ ኃይሎች የሰላም አማራጭ መቀበላቸውንም አንስተዋል።

በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ የልማት ሥራዎች እየተጠናቀቁ እየተመረቁ፤ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በባሕር ዳር፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና በሌሎች ከተሞች የመንገድ ላይ ደኅንነት ካሜራ በመግጠም ሰላማዊ እንቅስቃሴን ለማጽናት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ጎጃም እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች የጽንፈኛ ቡድኑ ከፍተኛ መሪዎች እና ታጣቂዎች የጥፋት ሕልም መክኗል።
Next articleየነዳጅ ማደያዎችን አገልግሎት በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚዘዋወረው መረጃ ልክ ነውን?