ለአፍሪካውያን በራሳቸው አቅም የአደጋ ስጋት ሥራዎችን መደገፍ የሕልውና ጉዳይ ነው።

11
አዲስ አበባ: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መጋቢት 30/2018 ዓ.ም እና ሚያዚያ 1/2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው 16ኛው የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም ጉባኤን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ.ር) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ስጋት ጉባኤ አህጉሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡ አደጋዎችን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ እንደሚኾን ይጠበቃል ብለዋል።
አፍሪካውያን ከውጭ በሚገኝ ዕርዳታ ላይ ብቻ ከመመስረት ይልቅ በራሳቸው አህጉራዊ አጋርነት እና ሉዓላዊ አቅም የአደጋ ስጋት ሥራዎችን በገንዘብ መደገፍ የሚችሉበትን አማራጭ መፈለግ የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል።
በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን የአደጋ ስጋት ተጽዕኖ ለመቋቋም የአባል ሀገራቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የጋራ አንድነት ወሳኝ መኾኑንም በመግለጫው አመላክተዋል።
ይህ ተቋም እ.አ.አ. በ2012 በአፍሪካ ኅብረት ስር የተመሠረተ ነው።
በአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የመንግሥት አገልግሎት ኀላፊ ኮፊ ኮኒን ዋና ዓላማውም አባል ሀገራት እንደ ድርቅ፣ ጎርፍ እና አውሎ ነፋስ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድመው እንዲተነብዩ እና በራሳቸው አቅም ምላሽ እንዲሰጡ መርዳት ነው ብለዋል።
ተቋሙ በተለይም ሀገራት ከአደጋ ጊዜ ዕርዳታ ጥበቃ ወጥተው ወደ ተሻለ ዝግጁነት እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ እንዲሸጋገሩ የሚያስችሉ አዳዲስ የአደጋ ሞዴሊንግ ስልቶችን ተግባራዊ ያደርጋል ነው ያሉት።
በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ያላትን ተሞክሮ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ልምዷን የምታካፍልበት እንደሚኾንም በመግለጫው ተነስቷል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ላይ ዋነኛው የውይይት አጀንዳ የተቋሙ የፋይናንስ ዘላቂነት ላይ ያተኮረ እንደሚኾንም ይጠበቃል።
ለዚህ ታላቅ ጉባኤ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን ጨምሮ 14 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በቅንጅት እየሠሩ እንደቆዩ እና ለጉባኤው ዝግጅት መጠናቀቁን በዚሁ መግለጫ ተገልጿል።
በጉባኤው ከ38 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከ300 በበላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፦ቴዎድሮስ ኅይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለውጡ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው።
Next articleለሀገረ መንግሥት ግንባታ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው።