ሰሙነ ሕማማት እና ምስጢሮቹ

12

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕማማት ሳምንት በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ እና ስቃይ የሚታሰብበት የጽሞና እና የአርምሞ ወቅት ነው።

ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሣኤ ድረስ የራሱ የኾነ ጥልቅ ትርጓሜ እና ታሪካዊ ይዘት እንዳለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕርዳር ሀገረ ስብከት የምሥራቀ ፀሐይ የይድበራ ማርያም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ እና የሐዲስ ኪዳን እና የፍትሐነገሥት መምህር መምህር ይኄይስ የሻምበል ተናግረዋል።

👉 ሰኞ፦ መርገመ በለስ

ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ ፍሬ ያልተገኘባትን በለስ የረገመበት ዕለት ነው። ይህች በለስ የኃጥያት ምሳሌ ተደርጋም ትወሰዳለች ብለዋል።

በለስ ሲበሉት እንደሚጣፍጥ ሁሉ ኃጥያትም ሢሠሩት ደስ የሚያሰኝ ቢመስልም እንኳ መጨረሻው ግን መራራ እና አስቸጋሪ መኾኑን መምህሩ አስረድተዋል። ይህም ጌታ ኃጥያትን ለማስወገድ የመጣ መኾኑን ያመላክታል ነው ያሉት።

👉 ማክሰኞ፦ የጥያቄ ቀን

አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን በተለያዩ ጥያቄዎች ሊያጠምዱት የሞከሩበት ዕለት ቢኾንም ጅማሮውን ያደረገው ከሰኞ ጀምሮ መኾኑን መምህሩ ገልጸዋል። “ይህን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ?” ለሚለው ጥያቄያቸው ጌታችን የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ናት ወይስ ከምድር? የሚል ጥበብ የተሞላበት ጥያቄ በመመለስ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።

👉 ረቡዕ፦ የፍርድ ቀን- ይህ ዕለት ሁለት ተቃራኒ ድርጊቶች የታዩበት እንደኾነ መምህሩ አስረድተዋል። በአንድ በኩል ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ለመስጠት ከአይሁድ ጋር የተመካከረበት እና ሴራው የተሳካበት ዕለት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ማርያም እንተ እፍረት (ኃጥያተኛዋ ሴት) ዋጋው እጅግ ውድ የኾነ ሽቶ በማፍሰስ እና በእንባዋ የጌታን እግር በማጠብ የኃጥያት ሥርየትን ያገኘችበት ነው ብለዋል። ይህም ክርስቶስ ኃጥያትን እንጂ ኃጥያተኛውን እንደማይጠላ ማሳያ ነው ብለዋል።

👉 ጸሎተ ሐሙስ፦ የትሕትና እና የኪዳን ቀን

በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ይህ ዕለት በሦስት ዋና ዋና ድርጊቶች ታስቦ እንደሚውል መምህሩ ገልጸዋል። የመጀመሪያው የሕጽበተ እግር ድርጊት ነው፤ ይህም ጌታ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ለሰው ልጆች ሁሉ የትሕትናን ታላቅነት ያስተማረበት ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ምስጥረ ቁርባን የተፈጸመበት ነው። ጌታ “ሥጋዬ ይህ ነው፣ ደሜም ይህ ነው” በማለት ለሐዋርያት ሥጋውን እና ደሙን የሰጠበት እና አዲስ ኪዳን የተመሠረተበት ዕለት እንደኾነም አንስተዋል።

ሦስተኛው ጸሎተ ጌቴ ሴማኒ ሲኾን ጌታ በጌቴ ሴማኒ የአትክልት ስፍራ የጸለየበት እና በሌሊት በአይሁድ እጅ የተያዘበት እንደኾነ ገልጸዋል።

በጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚከናወነው የቅዳሴ ሥርዓት አይሁድ ጌታን ለመያዝ ሲመጡ ያሳዩትን ዝምታ ለማስታወስ በለሆሳስ (ያለ ቃጭል እና ጽናጽል) እንደሚከናወንም የስብከተ ወንጌል ክፍል መምህሩ አስታውቀዋል።

👉 ዕለተ ዓርብ፦ የነጻነት አዋጅ

ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከዲያቢሎስ ነጻ ለማውጣት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነው። ዕለቱ የሕመም እና የሐዘን ቢኾንም የሰው ልጅ የነጻነት አዋጅ የታወጀበት በመኾኑ የደስታም ዕለት ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።

በወቅቱም ፀሐይ መጨለምን ጨምሮ ሰባት ታላላቅ ተአምራት ተገልጠዋል ብለዋል። ከእነዚህም መካከል ፀሐይ መጨለሟ፣ ጨረቃ ደም መምሰሏ፣ ከዋክብት መርገፋቸው፣ መቃብራት መከፈታቸው እና የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች መቀደዱ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

👉 ቅዳሜ፦ ቅዳም ሹር (የተሻረች ቅዳሜ)

ይህች ዕለት ጾም የታወጀባት በመኾኗ “የተሻረች” ትባላለች ነው ያሉት መምህሩ። በዕለቱ ካህናት ቄጠማ ይዘው በየቤቱ በመዞር የትንሣኤውን የምስራች ለምዕመናን ያበስራሉ ብለዋል።

በአጠቃላይ እነዚህ ዕለታት የሰው ልጅ ድኅነት የተረጋገጠባቸው እና የፈጣሪ ጥልቅ ፍቅር ለሰው ልጆች የተገለጠባቸው ታላላቅ መንፈሳዊ ዕለታት ናቸው።

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ ለውጡ በዘርፈ ብዙ ድሎች የታጀበ ነው።
Next articleለውጡ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው።