
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መጋቢት 24/ 2010 ዓ.ም የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰፍለፉ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ነው የተካሄደው።
በቦንጋ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ.ር) ሀገራዊ ለውጡ በዘርፈ ብዙ ድሎች የታጀበ መኾኑን ተናግረዋል።
መጋቢት 24 አካታች እና ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የተጣለበት፣ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው የሕግ ማሻሻያዎች የተደረገበት እንደኾነም ጠቁመዋል።
በለውጡ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መመዝበገባቸውን እና የዘመናት የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መመሥረትም የለውጡ አንዱ ትሩፋት ነው ብለዋል።
የተጀማመሩ የልማት እና የሠላም ግንባታ ተግባራት ከግብ እንዲደርስ ሕዝቡ በጽናት ከመንግሥት ጎን መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል። ምላሽ ያላገኙ የሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቁርጠኛ እንደኾኑም ተናግረዋል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሕዝብን አንድነት የሚፈታተኑ የውስጥ ባንዳዎችን በጽናት በመታገል የአፍራሽ ኀይሎችን ተልዕኮ በማክሸፍ ቀጣይ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
