
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ እንዲኾን በርእሰ መሥተዳድሩ የሚመራ ግብረ ኀይል በማቋቋም ለምርጫው አስቻይ ኹኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል። ለጸጥታ ኀይሎች ተደጋጋሚ ሥልጠና በመስጠት ያለምንም የጸጥታ ችግር የምርጫ ሂደቱ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የፖሊስ ተቋማት የምርጫ ሂደቱን፤ የመራጮችን፤ የእጩዎችን፤ የአስፈጻሚዎችን እና የምርጫ ጣቢያዎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ታጣቂ ኀይሎች የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ በማናጋት፤ ሕዝብን በመዝረፍ፤ የሀገር ሽማግሌዎችን በማጥቃት በሕግ የተመረጠ መንግሥትን ለማጥፋት በክልሉ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ ከጸጥታ አካላት እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመኾን የተቀናጀ ሕግ የማስከበር ሥራ በማከናወን ሰላምን ለማስከበር መሥራቱን ጠቁመዋል። አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መኖሩንም አንስተዋል።
ከምርጫ ቦርድ ጋር በመኾን በ143 የምርጫ ክልሎች በ12 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ በማድረስ፤ አሥፈጻሚዎችን በመመደብ ሰላማዊ ምርጫ እንዲከናወን እየተሠራ ነው ብለዋል።
ፓሊስ ገለልተኛ ተቋም ነው፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለም፤ የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ አይደግፍም ያሉት ኮምሽነር ጄኔራሉ በሕዝብ ምርጫ ሥልጣን ለያዘ መንግሥት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መኾኑንም ተናግረዋል።
✍️የፖሊስ ኀላፊነት ምንድን ነው?
👉የምርጫ ሂደቱን ሰላማዊ በማድረግ እና ኅብረተሰቡን በመጠበቅ የበኩላቸውን ሚና ይወጣል።
👉ገለልተኛ ምርጫ እንዲከናወን፤ ሕዝቡ ከዛቻ እና ማስፈራሪያ ወጥቶ በነጻነት ወጥቶ የሚፈልገውን እንዲመርጥ መደላድል ይፈጥራል።
👉 የምርጫ ኮሮጆን፤ የምርጫ ጣቢያዎችን፤ የመራጮችን፤ የተወዳዳሪዎችን የምርጫ ሂደት ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲኾን ኀላፊነት ወስዶ እንደሚሠራም አንስተዋል።
✍️ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል?
👉ማኅበረሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመኾን የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሠሩ ኀይሎችን የማጋለጥ ሥራ እንዲሠራ ይጠበቃል።
👉በምርጫ ሂደት ብቻ መንግሥት እንደሚቋቋም በማወቅ የምርጫ ካርድን በመያዝ የሚፈልገውን ፓርቲ መምርጥ ከማኅበረሰቡ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
