ጠንካራ ማኅበራዊ እሴቶች ለኢትዮጵያ አንድነት ዋልታ እና ማገር ናቸው።

2
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አብሮነት በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ውስጥ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶች ላይ የተገነባ የጸና መሠረት አለው። ይህ አብሮነት በደም፣ በኢኮኖሚ፣ በሃይማኖት፣ በሥነ ልቦና እና በባሕል ትስስሮች የተጋመደም ነው።
የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከባብረው እና ተደጋግፈው ይኖሩበታል። እንደ ዕድር፣ ደቦ እና የጋራ በዓላት ያሉ ማኅበራዊ እሴቶች ሕዝቡን በችግር እና በደስታ ጊዜ አስተሳስረው ቆይተዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር የሃይማኖት አባቶች አብሮነት እና ሌሎች እሴቶችን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደሴ ከተማ ቤተ ክህነት ተወካይ ሊቀ ትጉሃን ቆሞስ አባ ጸዳሉ ምንተስኖት የጥንት አባቶች በመደማመጥ እና በመከባበር የኢትዮጵያ ታሪክን እና አንድነትን ለትውልዱ ማውረስ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ፍቅርን አለማስቀደም፤ ለሰላም አለመትጋት፤ መከፋፈልን ማስቀደም፤ ዘረኝነትን ማቀንቀን እና እሴቶችን ማጥፋት አሁን ላይ ለሰላም እጦት መነሻ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በደሴ ከተማ የአረብ ገንዳ መስጊድ ምክትል ኢማም ሼህ ዑመር አሊ አንድነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቆ ቆይቷል ብለዋል። የራስን ጥቅም ማስቀደም የአብሮነት እሴቶቻችን አጥፍቷል ያሉት ሼህ ዑመር ሥልጣኔ እሴቶቻችንን ሊያጠፋ አይገባም ነው ያሉት።
ጠንካራ የማኅበረሰብ ትስስር እና ማኅበራዊ እሴቶች ለኢትዮጵያ አንድነት ዋልታ እና ማገር ኾነው መቆየታቸውን ያነሱት ደግሞ በኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ካውንስል የሰሜን ምሥራቅ ቅርንጫፍ ፕሬዝዳንት ፓስተር ዶክተር ቴዎድሮስ ጌታቸው ናቸው።
ሰው በማንነቱ የሚከበርበት፤ ሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጥበት፤ መደጋገፍ ጎልቶ የሚወጣበት እሴቶቻችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አጽንተው መቆየታቸውን ነው ያነሱት።
ሥልጣኔ የዘር ፖለቲካን በማስረጽ እሴቶቻችንን ሊያጠፋ አይገባም ያሉት ፓስተር ቴዎድሮስ በሃይማኖት ተቋማት አብሮነት፤ ፍቅር እና አንድነትን ይበልጥ በማስተማር የቀድሞ እሴቶቻችንን ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሥልጣኔን በመዋጀት የአብሮነት እሴቶችን ለዘላቂ ሰላም መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
መተዛዘን፤ መደጋገፍ፤ አብሮነት፤ መደማመጥን በማስቀደም እና የአባቶችን ምክር በመቀበል ፍቅር እና አንድነትን ማጽናት እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፋይዳ መታወቂያን ከባንኮች ጋር ማስተሳሰር ምን ጥቅም አለው?
Next articleበአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ የለውጡን ጉዞ የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።