
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የአዲስ ስፖርት ፓርክ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ልማት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ልማት ያለ ሰብአዊ ልማት ምልዑ ሊኾን አይችልም። የስፖርት መሰረተ ልማት ማስፋፊያዎቻችንም የዚሁ ተግባር ማሳያዎቻችን ናቸው። የመደመር መንግሥት እሳቤም ሁሉን አቀፍ ልማት ለዜጎቹ ተደራሽ ማድረግ ነው።
ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተመርቆ የተከፈተው እና በፈጣን አፈጻጸም ተገንብቶ የተጠናቀቀው የአዲስ ስፖርት ፓርክ የመደመር መንግሥት እሳቤ እና ተግባር የተገናኙበት የስፖርት አውድ መኾኑን ገልጸዋል።
ፓርኩ ዓለም አቀፍ ደረጃውቸውን የጠበቁ የሁሉም ስፖርቶች መሠረተ ልማት እና የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራን ባሟላ መልኩ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን አንስተዋል።
ፓርኩ ለወጣቶቻቾን መወዳደሪያ፣ ለታዳጊዎቻችን መጎልበቻ ከመኾኑ ባለፈ የስፖርት ፈርጦቻችን ሐውልት የቆመበት የጀግኖቻችን አምባ ነው ብለዋል።
በስፖርት ፓርኩ የጀግኖቻችን ገጽ ከነጽናታቸው፤ ከነብርታታቸው፣ ከነአርዓያነታቸው ፊታቸው ላይ ከተጻፈው የሀገር ፍቅር ጋር ተደምሮ ሐውልት ኾኖ ቆሟል ነው ያሉት። እነዚህ ሐውልቶች ለኢትዮጵያ የሮጡ እግሮች፣ ለሀገር ከተከፈለ ውድ ዋጋ እና ክብራቸው ጋር ተቀረጾ በክብር ተሰይሟል ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል አስምሮ፤ መንግሥት የመኾንን ኃላፊነት አክብሮ እየሠራ ስለመኾኑ ከሚመሰክሩ ተግባራት መካከል ዛሬ ተመርቆ ክፍት የኾነው የአዲስ ስፖርት ፓርክ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
ቃል ተግባር እየኾነ አዲስ አበባም እየተቀየረች፣ ኢትዮጵያም እየለማች፤ ወደ ክብር ማማ እየገሰገሰች ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
