
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ለ1ሺህ 224 ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ይቅርታ የተደረገላቸውን ታራሚዎች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የይቅርታ መስፈርቱን ላሟሉ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በክልሉ የይቅርታ አሰጣጥ መስፈርትን መሠረት በማድረግ በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በ2018 ዓ.ም በመጀመሪያ ዙር ይቅርታ እንዲደረግላቸው ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መጋቢት 18/2018 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ሥብሠባ ተወያይቶ መስፈርቱን ላሟሉ 1ሺህ 224 ታራሚዎች ይቅርታ እንዲደረግላቸው ውሳኔ አሳልፏል ነው ያሉት።
ታራሚዎች የይቅርታ መስፈርቱን አሟልተው በመገኘታቸው ይቅርታ የተደረገላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል።
ይቅርታ እንዲደረግላቸው ከቀረቡ ታራሚዎች መካከል 239 ታራሚዎች የይቅርታ መስፈርቱን አሟልተው ባለመገኘታቸው የይቅርታው ተጠቃሚ አለመኾናቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል።
ይቅርታ ከማያሰጡ ምክንያቶች መካከል የተፈጸመው የወንጀል ክብደት፣ ለተጎጅ ቤተሰብ ካሳ አለመክፈል እና ከተጎጅ ቤተሰብ ጋር እርቅ አለመፈጸም የሚሉት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ከአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የይቅርታ ተጠቃሚዎች ወደ ኅብረተሰቡ በሚቀላቀሉበት ጊዜ በልማት ሥራዎች፣ በማኅበራዊ እና በልዩ ልዩ መልካም ተግባራት ላይ መሳተፍ እና መተባበር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
