ከጣልቃ ገብ ደላላ የጸዳ ምርት ግብይቱ ጤነኛ፣ ዋጋውም መጠነኛ!

2

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተነ ይገኛል።

የደላላ ጣልቃ ገብነት እና ረጅሙ የግብይት ሰንሰለት ደግሞ ለምርቶች ዋጋ መናር እንደ ምክንያት ተደርገው ይነሳሉ። ይህንን የግብይት ስብራት ለመጠገን በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ እና በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የበጀት ድጋፍ የተገነባው የባሕር ዳር ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ይገኝበታል።

ማዕከሉ የፋብሪካ ምርቶችን ጨምሮ የምግብ ሰብሎችን፣ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ለሕዝቡ እያቀረበ ነው።

ሸማቾች ምርቶችን ከመደበኛው ገበያ ዋጋ በተሻለ እና በተመጣጣኝ ሁኔታ በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው።

ሀሳባቸውን ለአሚኮ ከሰጡት ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ወይንሸት አንተነህ እንዳሉት በማዕከሉ ሁሉም ዓይነት ምርቶች ተሟልተው መገኘታቸው ለነዋሪዎች ትልቅ እፎይታ ነው።

እንደ ሽንኩርት እና ቲማቲም ያሉ የዕለት ከዕለት ፍጆታዎች ከመደበኛ ነጋዴዎች እጅግ ባነሰ ዋጋ እየቀረቡ መኾኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከፋይዳው አኳያ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት በርካታ ፋብሪካዎች እና አምራቾች ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ከሻጮች መካከልም የዩኒሰን ዘይት ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት ታረቀኝ የገበያ መረጋጋትን ታሳቢ በማድረግ ምርቱን በቀጥታ በፋብሪካ ዋጋ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህ አሠራር ምርቶቹ ያለ ምንም ደላላ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ለተጠቃሚው እንዲደርሱ አስችሏል።

“ፋብሪካው የሚቀጥለው ተጠቃሚው ሲደሰት ነው” ያሉት ሥራ አሥኪያጁ፣ ለሸማቾች እርካታ ቅድሚያ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ገነት አሰፋ በምርቶች ያልተገባ የዋጋ ንረት ምክንያት የሚፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም አምራች እና ተጠቃሚን በቀጥታ የሚያገናኙ ሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላትን ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል።

ማዕከላቱ በዋነኛነት የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር እና ለሕዝቡ አማራጭ የገበያ ስፍራ ለመኾን ያለሙ ናቸው ብለዋል። በእነዚህ ማዕከላት 48 አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው እያደረሱ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።

የምርቶች ዋጋም የ15 በመቶ ቅናሽን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ነው ያረጋገጡት።

በከተማ አሥተዳደሩ የበጀት ድጋፍ የተገነባው ሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል ምርቃት ላይ የተገኙት አማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) ማዕከሉ ማንኛውም ዓይነት ምርት የሚገኝበት እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ እንደሚያቀርብም አረጋግጠዋል።
መሰል የገበያ ማዕከላትን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋፋት በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል።

ይህም በክልል ደረጃ የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተሰራጨው መረጃ የፈጠራ ወሬ ነው!
Next articleበግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።