
ባሕር ዳር: መጋቢት25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም አማካኝነት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የባዮሜትሪክ ማንነት ማረጋገጫ ሥርዓት የሀገሪቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረው ይገኛል።
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት የምዝገባ አሥተባባሪ ደጀኔ ገብሬ የባዮሜትሪክ ማንነት አንድ ሰው ከመወለዱ ጀምሮ ካሉት ተፈጥሯዊ መለያዎች ጋር የሚያስተሳስር እና ከሌላው ግለሰብ በልዩ ኹኔታ የሚለይበት አስተማማኝ መንገድ ነው ብለዋል።
አሠራሩ በዋናነት እንደ እጅ አሻራ፣ የዓይን ብሌን እና የፊት ገጽታ ያሉ የባዮሎጂካል መለያዎችን መሠረት በማድረግ የሚሠራ ነው። የ”ፋይዳ” መታወቂያ እነዚህን መረጃዎች ከግለሰቡ ሥነ ሕዝባዊ መረጃዎች ጋር በማጣመር ግለሰቡ በአንድ እና በአንድ መለያ ቁጥር ብቻ እንዲታወቅ ያደርገዋል።
ይህ ሂደት አንድ ሰው በራሱ ማንነት ላይ ሙሉ ቁጥጥር እንዲኖረው ከማስቻሉም በላይ ማንነትን በማጭበርበር የሚፈጸሙ ድብቅ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመግታት ትልቅ ፋይዳ አለው።
ሌላው የዚህ ቴክኖሎጅ ፋይዳ አገልግሎትን ማቀላጠፍ እና ለዜጎች ምቹ ኹኔታን መፍጠር ነው። ግለሰቦች የተለያዩ ሰነዶችን መያዝ ሳይጠበቅባቸው በአካላዊ አሻራቸው ብቻ ማንነታቸውን አረጋግጠው አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ።
ይህም በተመሳሳይ ፎቶ ወይም ሥም አማካኝነት በፋይናንስ እና በሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋሉ ማጭበርበሮችን እና ሥርቆቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ያስችላል።
ቴክኖሎጂው ከአንድ ጊዜ ብቻ ከሚያገለግል የይለፍ ቃል (OTP) የዲጂታል ማረጋገጫዎች በበለጠ ፈጣን እና አስተማማኝ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአኹኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባንኮች፣ የውል እና ማስረጃ ተቋማት እንዲኹም ሌሎችም መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለሠራተኞች መገኘት መቆጣጠሪያ እና ለደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ እያደረጉት ይገኛሉ።
ይህ ሂደት የመንግሥትን እና የግል ተቋማትን የአሠራር ግልጽነት ከማሳደጉም በላይ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት መሠረት እየጣለ መኾኑ ተመላክቷል።
ይኹን እንጂ ቴክኖሎጂው ከጥቅሞቹ ጎን ለጎን የራሱ የኾኑ ሥጋቶች እንዳሉትም አቶ ደጀኔ አልሸሸጉም። የመረጃ ደኅንነትን መጠበቅ እና የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥትም መረጃን እንደ ትልቅ ሀገራዊ ሀብት በመቁጠር ከፍተኛ ጥበቃ እያደረገ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኅብረተሰቡ የዲጂታል እውቀት እና የግንዛቤ ደረጃ ገና ያልዳበረ መኾኑ ሌላኛው ተግዳሮት ነው። ዜጎች ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀም እና ደኅንነት በቂ እውቀት ኖሯቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግ ቀጣይ የቤት ሥራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ የባዮሜትሪክ መታወቂያ ትናንት በወረቀት የታጠረውን ማንነት ዛሬ በአሻራ ወደሚፈታ ዲጂታል ቁልፍ የቀየረ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
