ድጋፍ የሚሹ ወገኖች

4

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተወልዳ ያደገችው በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ነው። በገንዳ ውኃ ሜዳዎች ከእኩዮቿ ጋር ቦርቃ አድጋለች። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በዚህው ከተማ ነው። የዛሬዋ ባለታሪካችን ወጣት ናርዶስ ጀምበሩ ትባላለች።

የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላም በማኒፋክቸሪንግ የትምህርት ዘርፍ የኮሌጅ ትምህርቷን ጀምራ ነበር። ተምራ የራሷን እና የቤተሰቦቿን ሕይወት የመለወጥ ጽኑ ምኞት የነበራት ናርዶስ የጀመረችውን የኮሌጅ ትምህርቷን ግን መቀጠል አልቻለም።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ቀለምን አይተው ዓለምን ቃኝተው ባልጠገቡ ዐይኖቿ ያልተጠበቀ እንግዳ ክስተት አጋጠማት። ብርሃን ናፋቂ የኾኑ ዐይኖች በሥጋ ተጋርደው ዓለምን በዕዝነ ልቦና እና በዐይነ ህሊና እንድትቃኝ ተገደደች። አንብበው ያልደከሙ የልጅነት ዐይኖች የብርሃን አድማስ ራቃቸው፤ ሠርተው ያልደከሙ፣ ብዕር እና ብራናን የጨበጡ እጆችም የአቅጣጫ መጠቆሚያ እንዲጨብጡ ተገደዱ። የወጣቷ ተስፋ እንቅፋት ተጋረደበት።

” የሁለተኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ እያለሁ ከባድ የራስ ምታት ያመኝ ነበር፤ በዚህ ምክንያትም ለዐይነ ሥውርነት እንድጋለጥ ኾኛለሁ፤ ከታመምሁ አሁን ስድስት ዓመት ኾኖኛል፤ የጀመርኩትን የኮሌጅ ትምህርቴንም በዚህ ምክንያት እንዳቋርጥ ተገድጃለሁ” ነው ያለችው።

ሠርቶ የመለወጥ ፍላጎት ይኑራት እንጅ የኢኮኖሚ እጦት እና በአካባቢው ምቹ መንገድ አለመኖሩ እንቅፋት እንደኾነም ተናግራለች። የጸጥታው ችግርም ቢኾን ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ፈታኝ መኾኑን አንስታለች።

ድንገት በደረሰባት የመኪና አደጋ ምክንያት ለዐይነ ሥውርነት የተዳረገው ሌላኛው የዚህው ከተማ ነዋሪ ወጣት ሁኔ ታፈረ ነው። ለዐይነ ሥውርነት የተዳረገው ገና በ21 ዓመቱ ነበር። በአጋጠመው ዐይነ ሥውርነትም ከፍተኛ የኾነ የሥነ ልቦና ጫና ሲደርስበት እንደነበር አጫውቶናል። ይሁን እንጅ አሁን ላይ በሥራ ተሰማርቶ ሕይወቱን ለመምራት ዐይነ ሥውርነቱ እንዳልበገረው ነው የነገረን።

በቂ ነው ባይባልም ከአሁን በፊት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እና ትብብር ሲደረግላቸው እንደነበር አስታውሷል። አሁን ላይ ግን ከግጭቱ ጀምሮ ” የት አላችሁ? ብሎ የሚፈቅደን እና ከጎናችን ኾኖ የሚረዳን አካል እንኳን የለም” ብሏል። ከአራት ዓመት በፊት የተሰጣቸው የአቅጣጫ መጠቆሚያ) መሳሪያ የሚቀይርላቸው አካል ባለማግኘታቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ መቸገሩን ገልጿል።

በመኾኑም መንግሥት እና በጎ አድራጊ ተቋማት በሚችሉት አቅም ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጠይቋል።

መምህር ጌታ ታደሰ የምዕራብ ጎንደር ዞን አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ናቸው። በዞኑ ከ2ሺህ 700 በላይ አካል ጉዳተኞች አሉ ብለዋል። ከእነዚህም 400 የሚኾኑት ተማሪዎች መኾናቸውን ጠቁመዋል። አሁን ላይ እነዚህ አካል ጉዳተኞች በከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ዊልቸር እና በዊት ጌን መሳሪያ እጦት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸውንም አስረድተዋል። በገንዳ ውኃ ከተማ በአካል ጉዳተኞች ማኅበር ለተደራጁ ወጣቶች በከተማ አሥተዳደሩ በኩል አንድ የኤሌክትሪክ ወፍጮ እና የመስሪያ ቦታ መሰጠቱን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ከ4 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገዬ ተናግረዋል።

በክልሉ የተረጋጋ ሰላም ባለመኖሩ አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች ለከፋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና ተጋላጭ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የጸጥታ ችግሩ በሎተሪ፣ ሊስትሮ እና በሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች በጎዳና ልመና እንዲሰማሩ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ገልጸዋል።

አሁን ላይ በርካታ አካል ጉዳተኞች በየቀኑ ወደ ማኅበሩ እየተቀላቀሉ መኾኑንም ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።

አሁን ላይ ያለው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እና እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተመጣጣኝ እንዳልኾነም ጠቁመዋል።

ከአሁን በፊት በክልሉ የነበሩ ረጅ ድርጅቶች በተወሰነ መልኩ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። ይሁን እንጅ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ዩኤስ አይዲን ጨምሮ በክልሉ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ረጅ ድርጅቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት አቁመዋል።

አካባቢው ሰላም ኾኖ አካል ጉዳተኞች ተገቢውን የሰው ሠራሽ አካል ድጋፍ ካላገኙ ኑሯቸው በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እየኾነ ነው ብለዋል።

በመኾኑም በጎ አድርጊ ድርጅቶች ወደ ክልሉ መጥተው የተለመደ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ በቅድሚያ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

የአካል ጉዳተኞች ችግር ጥልቅ፣ ውሥብሥብ እና አሳሳቢ መኾኑን በመረዳት ረጅ ድርጅቶችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ሁሉ ከጎናቸው ሊቆም እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዲስ የተሻሻለ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ የሕግ መድብል ጸደቀ!
Next articleበፎቶ ወይም ሥም አማካኝነት የሚስተዋሉ ሥርቆቶችን የሚያስቀረው የባዮሜትሪክ ማንነት ማረጋገጫ።