
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ለውጡን 8ኛ ዓመት በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊው ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥቅሞች፣ ዲፕሎማሲ እና በሌሎችንም ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ፖሊሲ በመደመር እሳቤ ላይ የተመሠረተ መኾኑን ገልጸዋል። የዲፕሎማሲ አቅጣጫው ኃይልን በማሰባሰብ፤ ወዳጅን በማብዛት እና በጋራ ጥቅም ላይ በትብብር መሥራት ላይ ያተኩራል ነው ያሉት። በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሠረተ ልማት እና በልማት ሥራዎች በቅንጅት መሥራት ለስኬታማነቱ ዋነኛ መሠረት ተደርጓል፤ ለዚህም የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
ፖሊሲው ከሀገራዊ ጥቅም ባሻገር የዜጎችን ክብር እና ሰብዓዊ መብት በማንኛውም የዓለም ክፍል ለማስከበር ቅድሚያ የሚሰጥ ዜጋ ተኮር መኾኑን ዶክተር ቢቂላ ጠቁመዋል።
መንግሥት የዜጎችን መብት እና ክብር የሚያስጠብቅ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሥርዓት መዘርጋቱንም ገልጸዋል። በተለይ ቀደም ሲል በሕገ ወጥ መንገድ በሚደረግ ስደት ይደርስ የነበረውን እንግልት ለመፍታት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሕጋዊ ስምምነቶች መደረጋቸውን ነው የገለጹት።
በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ እና ለሀገራቸው የዲፕሎማሲ አምባሳደር እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር በር ጥያቄ ታሪካዊ እና ሕጋዊ እውነታዎችን መሠረት ያደረገ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መኾኑን ኀላፊው አመላክተዋል።
ሀገሪቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ ማንንም በማይጎዳ መልኩ የባሕር በር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሠራች ትገኛለች ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣናም ለቀጣናዊ ትስስር ማጠናከሪያነት እየዋሉ እንደኾኑ ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።
“ዜግነት ሊቀየር ይችላል፤ እናት ግን አትቀየርም” ያሉት ዶክተር ቢቂላ ኢትዮጵያውያን የትም ቢኖሩ ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
የሀገር ውስጥ አንድነትን በማጠናከርም የውጭ ጣልቃ ገብነትን መመከት እና ሉዓላዊነትን ማስከበር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
