
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመኾን የዘርፉን ባለሙያዎች ለማብቃት የሚያስችል ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ እየሰጠ ነው።
ከቢሮው ጋር በጋራ የሚሠሩት የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎችም ከዘርፉ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት የሚያስችሉ ሥራዎችን በቅንጅት እንደሚተገብሩ አንስተዋል።
የፌዴራል ቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ከግብ ለማድረስ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ወደ ዘርፉ ማስገባት ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል።
በዚህም ከትብብር ባለፈ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የዘርፉን የሰው ኃይል በማሠልጠን በኩል የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ ባለሥልጣኑ የዱር እንስሳት በመጠበቅ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ እና የቱሪዝም ዘርፉን እያገዙ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች መኖራቸውን አንስተዋል። እነዚህን ጸጋዎች ከስነ ምሕዳር መጠበቅ ባለፈ ለቱሪዝም እድገት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና መጠቀም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰርፀ ፍሬስብሐት ኢትዮጵያ ትልቅነቷ የሚገለጽበት የራሷ የኾነ የፊደል እና የጽሑፍ ሃብት ያላት ሀገር ናት ብለዋል።
አማራ ክልልም የቀደምት አባቶቻችን አሻራ የኾኑ በርካታ የጽሑፍ ውጤቶች እና የሥልጣኔ መገለጫዎች የሚገኙበት አካባቢ መኾኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎትም የጽሑፍ ቅርሶችን መጠበቅ፣ የመዛግብት አያያዝ እና የባሕል ሃብቶችን ማደራጀት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
