
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሀገራዊ ለውጡን ጅማሮ የኾነውን መጋቢት 24 አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት የመላ ኢትዮጵያውያን ለውጥ የመሻት ፍላጎት ምላሽ ያገኘበት ዕለት ነው ብለዋል። የሁሉም ዜጋ ኅብረት የታየበት፤ ትብብርና አንድነት የተረጋገጠበት ዕለት ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ለውጡ ኢትዮጵያዊያንን በኅብረት አስተባብሮ በጋራ አሻግሯል፤ ሀገርንም አጽንቷል ነው ያሉት። ለውጡ ትናንትን እያደሰ፣ ዛሬን እየለወጠ ጠንካራ ሀገር የመገንባት ሕልሙን እና ትልሙን በተግባር እውን በማደረግ ስለመቀጠሉም አንስተዋል።
ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የሀገር እና የሕዝብን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል። የተጀመሩ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የሀገራችንን ከፍታ የሚያረጋግጡ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አብስሯል፤ በሁሉም የልማት ዘርፎች አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን ተግባራዊ በማድረግ የሀገራችንን የፖለቲካ አውድና ባሕል ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እድል ፈጥሯልም ነው ያሉት። ለውጡ ፈተናዎችን ወደ እድል የቀየረ፣ ወረትን ያዳበረ፣ የሀገራችን የቆየ አይበገሬነት ታሪክ ያረጋገጠ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ከጠመንጃ ይልቅ ምክክር እና ውይይትን፣ ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሐሳብ ብዝሃነትን በማስቀደም በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በትብብር አብሮ የመቆም አዲስ እሳቤን ፈጥሯል።
በመጭው ዘመንም ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ጠብቀን የጀመርነውን የሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በጋራ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
