55 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ ለግብይት ሊቀርብ ሲል መያዙን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

4

 

ጎንደር : መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የንግድ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱ በዋናነት የነዳጅ አቅርቦት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።

የቶታል መገጭ ማደያ ሱፐርቫይዘር ዳንኤል ምንተስኖት ነዳጅ የሚጭኑ ቦቲዎች የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ለሥራ እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል። ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለመከተል በቴሌ ብር አገልግሎት እየሰጡ መኾኑንም ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ታደሰ ገላው በነዳጅ እጥረቱ ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በመለየት ለመፍትሔው እየተሠራ ነው ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ የነዳጅ አቅርቦቱ በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የነዳጅ እጥረት የሚፈጥሩ አካላትን በመለየት የክትትል እና ድጋፍ ሥራን ከንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው ብለዋል። ‎

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን ነዳጅ የጫኑ ቦቲዎች ከቦታ ቦታ እንዲቀሳቀሱ እና አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሰላም ተግባሩ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ከነዳጅ ታሪፍ በላይ በሚሸጡ ማደያዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ነዳጅን በአግባቡ ለመጠቀም ተቋማት የተሽከርካሪዎች ሥምሪትን በአግባቡ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አማካሪ መሐመድ ጀማል (ዶ.ር) በሕገ ወጥ መንገድ ሲሳተፉ የተገኙ ነጋዴዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ላይ አስፈላጊው ቅጣት እየተላለፈ ነው ብለዋል።

እስካሁን ከ90 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

በክልሉ እስካሁን በሕገ ወጥ መንገድ ለግብይት ሊቀርብ የነበረን 300 ሺህ ሊትር ናፍጣ፣ 155 ሺህ 363 ሊትር ቤንዚን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋሉንም ተናግረዋል። ይህም በገንዘብ ሲተመን 55 ሚሊዮን ብር ይኾናል ነው ያሉት።

ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል።

ዘጋቢ :- አዲስ አለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት የተቀናጀ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleአስተማማኝ የምግብ ሉዓላዊነትን ለመገንባት የግብርና ኢንቨስትመንትን ማዘመን ይገባል።