
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት የሰላም ጋሻ፣ የብሔራዊ ክብር እና ጥቅማችን ዘብ ናቸው ብለዋል።
ዛሬ “የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ቅንጅት ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፍረንስ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
በቀጣናችን የሚስተዋሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች፣ የአሸባሪ ቡድኖች ሴራ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ሀገራችንን ቢፈትኑም፤ በጸጥታ እና ደኅንነት ተቋሞቻችን ጥንካሬ እና በልጆቿ መስዋዕትነት ለአፍሪካ ፋና ወጊ የሚኾን ተግባር በመፈጸም ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ ጸንታ ቆማለች ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የጸጥታና ደኅንነት ተቋሞቻችን ችግርን ወደ ዕድል እንዲቀየሩ ያስቻሉ ናቸው፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት የዘመኑት የጸጥታ ኃይሎቻችን ሌት ተቀን ትጋት እና በሕዝባችን አጋርነት ሀገራዊ ሁለንተናዊ ውጤት ማስመዝገብ ያስቻለን ነው።
ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር የምናደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴዎች ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡ ይህን ስኬት ለማስመዝገብ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የፌደራል የጸጥታ እና ደኅንነት፣ የክልል የጸጥታ ተቋማት ቅንጅትና የጋራ ጥረት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ነው ያሉት።
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሰላምን ለማስፈን የተሄደባቸው ርቀቶችና የተገኙት ውጤቶች የሚበረታቱ መኾናቸውን ገልጸዋል። በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማትና የሕዝቡ የተቀናጀ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ የምናካሂደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ዴሞክራሲን የምናጸናበት ታሪካዊ ምዕራፍ እንዲኾን የጸጥታ ተቋሞቻችን ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ እምነቴ የጸና ነው ብለዋል።
ጉዟችን ተጀመረ እንጂ አልተቋጨምና ከትናንት ዕዳዎች ተላቀን፣ የዛሬ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ለነገው ትውልድ የምትመጥን ሀገር ለመገንባት በዓላማ ጽናት እንቀጥላለን። ለሀገር ሕልውና መስዋዕትነት ለከፈሉና ሌት ተቀን ለሚተጉ የጸጥታ እና ደኅንነት መሪዎች እና አባላቶቻችን፣ በሀገሩ ጉዳይ ለማይደራደረው ለጀግናው ሕዝባችን ያለኝን ጥልቅ አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
