የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት በትኩረት እየተሠራ ነው።

3

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት እና ለሁለንተናዊ ዕድገት በሚል መሪ መልዕክት ለቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ባለድርሻ አካላት የሥልጠና እና የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ ስለሽ ግርማ ባለፉት ዓመታት ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ነው ብለዋል። በዚህም በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች መገንባታቸውን አንስተዋል።

ለረጅም ዘመናት አደጋ ተጋርጦባቸው ለቆዩ ታላላቅ ቅርሶች የጥገና ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ የሰው ኀይል ማሠልጠን መቻሉንም ገልጸዋል።

በፊት የተገኙትን ስኬቶች አጠናክሮ በማስቀጠል በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ውጤታማ ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ የአማራ ክልል የበርካታ ቋሚ እና ተንቀሳቀሳሽ ቅርሶች ባለቤት ነው ብለዋል። እነዚህ ቅርሶች ለክልሉም ኾነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መለያ በመኾን ጥንታዊነትን፣ ታሪካዊነትን፣ ቀደምትነትን እና ታላቅነትን ሲያንጸባርቁ የኖሩ እና የሚኖሩ እውነተኛ ምስክሮች ናቸው ነው ያሉት፡፡

የቱሪዝም ዘርፍ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት በትኩረት ተይዞ እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም ለመቀየር የሁሉንም ቅንጅት ይጠይቃል ነው ያሉት። ለዚህም ከፌዴራል እና ከክልል ተቋማት ጋር በቅንጅት ሢሠራ መቆየቱን አንስተዋል። በመዳረሻ ልማት እና በቅርስ ጥገና ሥራዎች ዙሪያም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ለባለሙያዎች፣ በየደረጃው ላሉ የዘርፉ መሪዎች እና ለባለድርሻ አካላት አቅም ለማሳደግ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል። የዘርፉን ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ፣ በመረጃ አያያዝ እና በዘመናዊ የቱሪዝም አገልግሎት ዙሪያ ለማብቃት አስተዋጽኦ እንዳለውም አንስተዋል።

የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ግንዛቤ ለማሳደግ፣ የቅርሶችን ዝርፊያ እና ውድመት ለመከላከል፣ በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር ያለመ መኾኑንም አንስተዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ከዞኖች፣ ከከተማ አሥተዳደሮች እና ወረዳዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ መሪዎች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ :- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሴፍቲኔት የኢኮኖሚ መነሻ እንጅ የእርዳታ መለማመጃ አይደለም።
Next articleየአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር በልማት የተሳሰረ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እየተሠራ ነው።