
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር እና የተጨማሪ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ምረቃ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
ፕሮግራሙ ባለፉት ሦስት ዓመታት 3 ሺህ 685 የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉም ተገልጿል።
በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ተጠቃሚ የኾኑ ግለሰቦች የሴፍትኔት ፕሮጀክት ተጠቃሚ ከመኾናቸው በፊት በድህነት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል። የሥራ ተነሳሽነት እና ሃሳብም እንዳልነበራቸው አስታውሰዋል።
በመርሐ ግብሩ ተሳታፊ ከኾኑ በኋላ ግን በኢኮኖሚ፣ በኑሮ እና በአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ ነው የገለጹት። በሴፍቲኔት ባገኙት ሥልጠና እና የገንዘብ ድጎማ ሥራ በመፍጠር ኑሯቸውን ማሻሻል እንደቻሉም ተናግረዋል። ልጆቻችንን ሳንቸገር እያስተማርን ነውም ብለዋል።
እርዳታ መጠበቅ አስፈላጊ አይደለም ፤ ሴፍቲኔትን እንደ መነሻ መጠቀም እንጅ እርዳታ መለማመጃ ማድረግ አይገባም ነው ያሉት።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት ሥራ አስኪያጅ ተሻገር አዳሙ በሁለተኛው ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ባለፉት ሦስት ዓመታት 3 ሺህ 686 የቤተሰብ ተጠሪዎች፤ 11 ሺህ 883 ደግሞ በአካባቢ ልማት እና በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ንዑስ ፕሮግራም ተሳታፊ የኾኑ ግለሰቦች ለምረቃ መብቃታቸውን ገልጸዋል።
ለተጠቃሚዎች 248 ሚሊዮን 335 ሺህ በላይ ብር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማ አሥተዳደሩ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በሴፍቲነት ፕሮግራም መታቀፍ ያለባቸው በርካታ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መኾን እንደቻሉ ተናግረዋል
የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን የወደፊት እጣ ፈንታ በተሻለ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የሥራ ልምድ ቀስመዋል ነው ያሉት። ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች በመሳተፍም ሃብት የማግኘት አቅማቸውን አሳድገዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የክልሉ ልማታዊ ሴፍቲኔት ስትሪም ኮሚቴ አባል መሠረት አዱኛ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ በ18 ከተሞች እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ልማታዊ ሴፍቲኔት ቁጠባን መሠረት ያደረገ የሃብት አሥተዳደርን እና አጠቃቀምን ለተጠቃሚዎቹ አስተምሯል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
