የ2018/2019 የመኸር ምርትን ስኬታማ ለማድረግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች እየቀረቡ ነው።

6

 

አዲስ አበባ: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የግብርና ሚኒስቴር የ2018/2019 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት የሰብል ልማት ንቅናቄ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ እየተከናወነ መኾኑን አስታውቋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) የምርት ዘመኑን የንቅናቄ መድረክ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የዘንድሮው የመኸር እርሻ ንቅናቄን ለማሳካት በሀገር እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችን በዓይነት እና በጥራት ማሳደግ ላይም ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚኾኑ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ላይም እየተሠራ እንደኾነ አብራርተዋል።

ለምርት ዘመኑ አስፈላጊ የኾነውን 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት ታቅዶ እስካሁን 14 ሚሊዮን ኩንታሉ አስቀድሞ ግዥ ተፈጽሟል ነው ያሉት።

ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ካለው ጦርነት ተፅዕኖ ነፃ በኾነ መልኩ ያለምንም ስጋት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ አስችሏል ብለዋል። ወደብ የደረሰውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማድረስም የባቡር ትራንስፖርትን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ከፌዴራል እና ከክልል መንግሥታት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ማቆሟን የጠቀሱት ሚኒስትር ድኤታው የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ተናግረዋል።

በ2017 ዓ.ም በመኸር ስንዴ ልማት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በስንዴ በመሸፈን 175 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል።

የ2018/2019 የመኸር እርሻን ስኬታማ ለማድረግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች እየቀረቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። አርሶ አደሮችን፣ ባለሙያዎችን እና መሪዎችን የማዘጋጀት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

በንቅናቄው የፌዴራል እና የክልል የግብርና የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ መኾናቸው ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመንግሥት ዜጎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለማሽጋገር እየሠራ ነው።
Next articleሴፍቲኔት የኢኮኖሚ መነሻ እንጅ የእርዳታ መለማመጃ አይደለም።