
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እ.አ.አ በ 2022 የወሎ ዩኒቨርሲቲ የጤና ዘርፍ ምሁራን “ፕሎስ ዋን” በተሰኘው ዓለም አቀፍ ታዋቂ መጽሔት ላይ “በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በደሴ ከተማ ለጤና ጠንቅ የኾነ የትራፊክ ድምጽ ብክለት ስርጭት” በሚል ርዕስ ባሳተሙት አንድ ጽሑፍ ከመጠን ያለፈ ጩኸት ወይም ጫጫታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሥራ ላይ ጤና ጠንቅ መኾኑን አስፍረዋል። ማኅበራዊ እና አካላዊ ጉዳቶችን እንደሚያስከትልም ጠቅሰዋል።
የሰዎችን የመስማት ችሎታን በመቀነስ፤ ለልብ እና ለደም ዝውውር በሽታዎች በማጋለጥ፤ የልጆችን የአዕምሮ ዕድገት በመግታት፤ እንቅልፍ በማዛባት የጤና እና የሥነ ልቦና ችግሮች እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
ተሽከርካሪዎች፣ ምሽት ቤቶች፣ የድምጽ ማጉያዎች፣ አነስተኛ ፋብሪካዎች፣ የከተሞች መስፋፋት እና ሌሎች የድምጽ ብክለቱ መንስኤ መኾናቸውንም ጽፈዋል።
በአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ እና ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ ዳይሬክተር አብረሃም ማርዬ ብክለት ከሚቃጠሉ ነገሮች፣ ከፕላስቲክ እና ከድምጽ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
ድምጽ አልባ ገዳይ የሚባለው ብክለት ከልክ ያለፈ ድምጽ ነው ብለዋል። የድምጽ ብክለት ጉዳቱ ብዙም ትኩረት ባይሰጠውም አካባቢን እና ማኅበረሰብን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል ነው ያሉት።
የድምጽ ብክለት ማኅበራዊ ቀውስ ይፈጥራል ያሉት ዳይሬክተሩ ተስማምተው ይኖሩ የነበሩ ጎረቤቶች እንዲጣሉ፤ በየአካባቢው የሚገኙ ፋብሪካዎች ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲጋጩ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
የድምጽ ብክለት የሚፈጥሩ ነዳጅ የሚጠቀሙ እንደ ጋራዥ፣ ፋብሪካ፣ ወፍጮ እና መሰል ነገሮች ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ኀይል መጠቀም ሲሸጋገሩ ድምጹን በመቀነስ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ከተሞች ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች የሚያወጡት ከመጠን ያለፈ ድምጽ ከፍተኛ የድምጽ ብክለት ይፈጥራል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መጠቀም ደግሞ የድምጽ ብክለትን ለመከላከል ዋነኛው መፍትሔ ነው ብለዋል።
ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ነገሮችን በኤሌክትሪክ ኀይል መተካት የድምጽ ብክለትን በከፍተኛ ደረጀ ይቀንሳል ነው ያሉት። ጤናን ለመጠበቅ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር እና ምቹ የመኖሪያ ከባቢን ለመፍጠር እንደሚረዳም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
