ኢትዮጵያ ዐዲሲቷ የተስፋ ዓድማስ ናት።

10
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባጋራው መረጃ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ የታሪክ አውድ ውስጥ አዲስ ትርጉም እና ጽኑ ቃል ኪዳን ተላብሶ ብቅ ያለ፣ ለሀገራችን እና ለሕዝቦቿም አዲስ የተስፋ አድማስን የፈነጠቀ ክስተት ነበር ብሏል።
ይህ ዕለት ኢትዮጵያን ተብትቦ ይዞ ከነበረው ውስብስብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቅርቃር አውጥቶ ወደ ብሩህ መጻኢ ዕድል ለማሸጋገር የተገባ ታላቅ የትውልድ ውል ኾኖ ተመዝግቧል።
ከመጋቢት 2010 ዓ.ም እስከ መጋቢት 2018 ዓ.ም ባሉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የጊዜ ጉዞ ውስጥ፣ ሀገራችን ያስመዘገበቻቸው ድሎች፣ የተሻገረቻቸው ክፉ ፈተናዎች እና የገነባቻቸው ተጨባጭ እውነታዎች ኢትዮጵያን ከነበረችበት የውድቀት ስጋት ታድገው ወደ ላቀ የልዕልና ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው። ይህ የትንሣኤ ጉዞ በፈተና እቶን ውስጥ አልፎ የነጠረ፣ በጽናት የታነጸ እና የኢትዮጵያን የማይበገር ማንነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዳግም ያስመሰከረ የታሪክ አሻራ ነው።
የዛሬው የፖለቲካ ምኅዳራችን አስኳል የተቀዳው ከዚሁ ከመጋቢት 24ቱ የታሪክ ብርሃን ነው። የሐሳብ ልዩነትን በጸጋ የሚቀበል፣ የመሐል እና የዳር ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን በማክሰም ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ያጸና፣ ከፋፋይና ነጠላ ትርክቶችን በማርገብ የወል ሀገራዊ እሴቶችን የሚያሰርጽ ሥርዓት ዕውን ኾኗል። ብሔራዊ ጥቅምን እና ደኅንነትን የሚያስቀድም፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን የሚከተል እና ለጎረቤት ሀገራት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጥ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር መሠረቱ የተጣለውም በዚህ ወቅት ነበር። ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ የፖለቲካ ዓውዱ በዘላቂነት እንዲጸና አካታች ሀገራዊ ምክክር በስፋት እየተካሄደ ከመኾኑም በላይ የሽግግር ፍትሕ ለማስፈንም እየተሠራ ይገኛል፡፡
የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ራሳቸውን በራሳቸው የማሥተዳደር መብታቸውን በተግባር እየተለማመዱ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በነፃነትና በሕግ አግባብ ራሳቸውን ለውድድር እያቀረቡ ይገኛሉ። መንግሥት አካታች የፖለቲካ ስርዓት እንዲሰፍን በወሰደው ብስለት የተሞላበት እርምጃ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ከካቢኔ ጀምሮ በየደረጃው ሥልጣን እያጋራና ሀገር በጋራ የመምራት ዕድል እየሰጠ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያውያን በለውጡ ብሥራት አማካኝነት ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ መተባበር የዲሞክራሲ ልምምድ መሸጋገራቸውን በግልጽ ያሳያል።
መጋቢት 24 የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስብራት የታከመበት እና አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የተጀመረበትም ጭምር ነው። ሀገራችን በተለያዩ የንግድ ብድሮች ጀርባዋ ጎብጦ፣ በነጠላ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት የመልማት ጸጋዎቿ ተዳፍነው፣ በመንግሥት የአፈጻጸም ዐቅም ውስንነትም በብሔራዊ ውርደት ዋዜማ ላይ ቆማ ነበረ። የለውጡ መንግሥት እነዚህን አደገኛ ቅርቃሮች በመበጣጠስ ኢትዮጵያን አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ማድረግ ችሏል። አዳዲስ የንግድ ብድሮችን ከመውሰድ በመቆጠብና የነበሩትንም በእልህ አስጨራሽ ድርድሮች ወደ ተራዘመ የክፍያ ጊዜ በመቀየር ኢኮኖሚውን ከውድቀት ታድጓል።
በየደረጃው በተተገበሩ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ከግብርና መር ወደ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትኩረት በመዞሩ የሀገሪቱን ጸጋዎች በላቀ ደረጃ መጠቀም ተጀምሯል። እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ካጋጠሟቸው መዋቅራዊ እና የአፈጻጸም ችግሮች ወጥተው ዓለምን ባስደመመ ተአምር ለምርቃት በቅተዋል። ከሕዳሴው ግድብ ጎን ለጎን በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅም ኢትዮጵያ በአዲስ የኢኮኖሚ ምሕዋር ውስጥ መግባቷን ለዓለም አሳይታለች። ይህም ሀገሪቱ ያላትን ታሪካዊ የነፃነት ቀንዲልነት ከኢኮኖሚ ልዕልና ጋር አጣምሮ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ተሰሚነቷ እንዲጎላ አድርጎታል። ዛሬ ኢትዮጵያ በጥቂት መሪዎች የምትጎበኝ ሀገር ሳትኾን፣ በየሳምንቱ የታላላቅ ሀገራት መሪዎችን የምታስተናግድና ዲፕሎማሲዋ ከተከላካይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት ያደገባት ኃያል ሀገር ኾናለች።
በተመሳሳይ መልኩ መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ከተሞች ዳግም የተወለዱበት መነሻ ኾኖ ያገለግላል። የለውጡ መንግሥት ከተሞችን ወደ ዘመናዊነት በማሸጋገር ንጹሕ፣ ስሉጥ አገልግሎት ሰጪና የተቀናጀ መሠረተ ልማት መገኛ እንዲኾኑ በትጋት ሠርቷል። በኮሪደር ልማት አማካኝነት ከተሞች አዲስ ገጽታን ተላብሰዋል። ዘመናዊነትን የሚኖርና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታነጸ ትውልድ የመቅረጽ ሥራ ጥልቅ መሠረት ይዟል። ከዚህም ባለፈ ማኅበራዊ መስተጋብር ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲጠናከር፣ ብዝኃነት የሀገር ጌጥና አንድነት ደግሞ የሀገር ዐቅም እንዲሆን ተደርጓል።
ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን በጋራ የመጋፈጥ ባሕል ጎልቶ ታይቷል። በድርቅ እና በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች የተደረገው ሀገራዊ ድጋፍ የዚሁ ጽኑ አንድነት ማሳያ ነው። የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ ከባዕዳን ጋር አብረው ግጭት ለሚፈጥሩ ባንዳዎች፣ መላው ሕዝብ በአንድነት ቆሞ ምላሽ የሰጠበትና ጀግናው መሪም እንደ ቀደሙት አባቶቻችን ለሀገር ክብር ወደ ጦር ሜዳ የዘመተበት የታሪክ ምዕራፍ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በኃይል እና በምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ አስደማሚ ስኬቶችን አስመዝግባለች።
በታዳሽ ኃይል ልማት ለዓለም አብነት መኾን ችላለች። ቀድማ ወደ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች መሸጋገሯ አሁን ያለውን የነዳጅ ቀውስ በተወሰነ ደረጃ እንድትቋቋም ረድቷታል። ምንም እንኳን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ጉዞዋን ለማዘግየት ቢሞክሩም፣ ኢትዮጵያ ግን አሁንም በአስተማማኝ የፖሊሲ አቅጣጫ ላይ ትገኛለች።
እያደገ በመጣው ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖዋ፣ እየፈረጠመ ባለው ኢኮኖሚዋና በጀግኖች ልጆቿ ጽናት፣ ሀገራችን አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ኾና ትቀጥላለች። ዛሬ ላይ የለውጡን መሠረት ከማስፋትና ከማጽናት ወደ ማላቅ የተሸጋገረችው ኢትዮጵያ፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌትነቷን በተግባር ታውጃለች። ይህን ለውጥ እውን ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ በድል እንደሚያሳርጉት ጥርጥር የለውም ብሏል በመልዕክቱ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
Next articleበኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።