“መጋቢት ለፖለቲካችን የልዩ ታሪክ ወር ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

8
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የጠራ ሰማይ በሚታይበት፤ የድካም አዝመራ በሚሰበሰብበት የመጋቢት ወር፣ አሻጋሪ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ከፍታዎቻችን አስምረናል ብለዋል።
መጋቢት ለፖለቲካችን የልዩ ታሪክ ወር ነው፡፡ ሕዝብ ከጨለማ ወደ አሻጋሪ ብርሀን የወጣበት የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ወርም ነው። በመጋቢት አያሌ የለውጥ ነጋሪቶች ተጎስመው አዲስ የፓለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ ታውጇል ነው ያሉት።
ሕዝባዊ ግፊት እና ትግል ያመጣው የመጋቢት ለውጥ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ያስቀሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ስብራቶችን መጠገን ያስቻሉ ሪፎርሞች የተተገበሩበት ነው፤ የሕዝባችን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት የጀመሩበት አዲስ የኢትዮጵያ ንጋትም ኾኗል ብለዋል።
የምርት እና ምርታማነት ዕድገት፣ የቱሪዝም መነቃቃት፣ የማዕድን ሃብት ተጠቃሚነት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ የከተማ ልማት እና የዲፕሎማሲ ስኬት ሁሉ ጅማሯቸው መጋቢት ነው፡፡
በተቋም ግንባታም ባለፉት ስምንት ዓመታት አስደናቂ ለውጦች ተመዝግበዋል። የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ታላቋን ኢትዮጵያ የሚመጥኑ እንዲኾኑ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀትና በሥራ ከባቢ የማዘመን ሥራዎች በስኬት መከናዎናቸውን ገልጸዋል።
መጋቢት የሀገራችንን ከተሞች የማዘመን ትልም ዕውን የኾነበት፣ የኮሪደር ልማት ስኬቶችን መጎናፀፍ የቻልንበት፣ የዓየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያለመ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻን በቢሊየን የሚቆጠሩ ዛፎችን በመትከል አረንጓዴ ምድር የፈጠርንበት፣ በሀገራችን አዲስ የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲ እና የትርክት ዕይታ የተበሰረበት ወር ነው ብለዋል።
ለሺህ ዓመታት በዝናብ ጥገኝነት ላይ ተመስርቶ የነበረውን ግብርናችንን በማዘመን በበጋ መስኖ ዓመቱን ሙሉ ማምረት የጀመርነው በዚሁ ወርሃ መጋቢት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ኢኒሼቲቭ ከውጭ የሚገባ ስንዴን ሙሉ ለሙሉ በማቆም አሁን ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር ኾናለች። የወተት፣ የዶሮና የማር ምርቶች በየቤተሰቡ ሌማት ላይ እንዲገኙ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ጅማሮው መጋቢት ነው፡፡
እነዚህ ባለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያን ከውስብስብ ችግሮች በማላቀቅ ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ ካሸጋገሩ ድሎች ጥቂቶቹ ናቸው።
ለሕዝባችን የላቀ ተጠቃሚነት፣ ለሀገራችን ክብር እና ብልጽግና መሳካት አበክረን እንሠራለን ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዐይን ሲሰወር ልብ በርቶ የሚገልጣቸው ጥበበኛ እጆች አሉ።
Next articleበአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።