
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት ትዕግስት ስንታየሁ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናት። ገና በልጅነት ዕድሜዋ ነበር የዓይኖቿን ብርሃን ያጣችው። ዓይነ ሥውርነት ሳይገድባት ግን የአንገት ፎጣ፣ ኮፍያ እና ባሕላዊ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃ ስፌት ትሠራለች።
አሁን ላይ የ12ኛ ክፍል የሪሚዲያል ትምህርቷን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተከታተለችም ትገኛለች።
ኑሮን ለመቋቋም አልፎ አልፎ በባሕር ዳር ውብ ጎዳናዎች ጠርዝ የሚዛን ሥራም ትሠራለች። ሲገኝም አጫጭር ሥልጠናዎች ላይ እንደምትሳተፍም አጫውታናለች። ሁለገብ ክህሎት እንዲኖረኝ ነው የምፈልግ የሚል ጽኑ አቋምም አላት።
ከራሷ አልፎ ለብዙዎች ተስፋ የሚዘራ ሃሳብ ያላት እና የኢኮኖሚ ጥገኛ ላለመኾን በብዙ መልኩ እየተንቀሳቀሰች የምትገኝም ናት።
የመሥሪያ ቦታ እና የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ቢመቻችላት ደግሞ ክህሎቷን ወደ ገንዘብ የሚቀይር ሥራ መሥራት እንደምትፈልግ ነው የገለጸችልን።
ለሥራ እንጂ ለልመና እጄን አልዘረጋም ነው ያለችን። ለአካል ጉዳተኞች የሚደረጉ እገዛዎችም ዘላቂ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንጂ ጊዚያዊ እርዳታ ሊኾኑ እንደማይገባ ገልጻለች።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የሴቶች ዘርፍ አሥተባባሪ ሰውሀረግ ጌታቸው በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዚህም ቋሚ እና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የኾኑ አሉ ነው ያሉት።
በቀጣይም በተለይም ሴት አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ይሠራል ነው ያሉት። ለዚህም የአጋር አካላት እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዳይሬክተሩ ስላባት ሰውአገኝ እንዳሉት በስምንት ወራት ውስጥ ለ1ሺህ 974 አካል ጉዳተኞች ቋሚ እና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ከነዚህ መካከል 1ሺህ 523 የሚኾኑት ዘላቂ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው ነው ያሉት።
በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ሥራ ከጀመሩት ውስጥ 152 ለሚኾኑት የገብያ ትስስር መፍጠር እንደተቻለም ጠቅሰዋል። 356 ለሚኾኑት በሼድ አቅርቦት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ልዩ ክህሎት ያላቸውን አካል ጉዳተኞች በልዩ ሁኔታ ሥልጠና የሚሠጥበት የአሠራር ሥርዓት እንዳለም ገልጸዋል።
ለዚህም የሚኾን የሥልጠና ማዕከል ተዘጋጅቷል። ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ ፍላጎታቸውን እና አቅማቸውን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
