
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጅ ቀርጻ እየሠራች ነው። የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ እና የአየር ብክለትን በመከላከል ኢኮኖሚዋን ለማሳደግም አልማለች። ከእነዚህም ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ እና ማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ዳይሬክተር አብረሃም ማርዬ ከመሬት በላይ ከሚገኙ የተለያዩ የኃይል ምንጮች መካከል ከውኃ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል አንደኛው ነው ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የውኃ ሃብት ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም አላቸው። ከውኃ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ ታዳሽ እና ዘላቂ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ የውኃ ሃብት ታዳሽ ኃይልን በስፋት እንድትጠቀም ያስችላታል ነው ያሉት። የኤሌክትሪክ ኃይልን በተለይ በትራንስፖርት ዘርፍ መጠቀም የካርቦን እና ሚቴን ልቀትን በመቀነስ የአካባቢ ብክለት ሙሉ በሙሉ ለመከላከል ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
በዚህ የተነሳም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን መጠቀም ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እና ተቀባይነት ያገኘ ነው ብለዋል።
ብዙ ሀገራት በተለይ ነዳጅ አምራች የኾኑት የውኃ ኃይል ስለሌላቸው ታዳሽ ኃይል የማመንጨት እኩል ዕድሉ የላቸውም ያሉት ዳይሬክተሩ ነዳጅ መጠቀም እና መሸጥ ብቸኛ አማራጫቸው እንደኾነ አንስተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳሽ ኃይልን የመጠቀም መብት እና አቅም ያላቸው ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚጠቀሙ ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም አማራጫቸው መኾኑንም ተናግረዋል።
ሌሎች ሀገራት ነዳጅ ሽጠው ኢኮኖሚያቸውን አሳድገዋል፤ ኢትዮጵያም ውኃዋን ተጠቅማ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ይገባታል ነው ያሉት።
የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መተካት ያለው ጠቀሜታም ከፍተኛ ነው ብለዋል። በከሰሞኑ እንደተፈጠረው የነዳጅ መስተጓጎል ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍቻ አንደኛው መንገድ ነውም ብለዋል። ለነዳጅ የምታወጣውን ወጭ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ነው ያሉት።
የአየር ብክለትን ከመከላከል አኳያ ፋብሪካዎችም የኤሌክትሪክ ኃይልን እንዲጠቀሙ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ነው ያነሱት።
መንግሥት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መለዋወጫ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም አመላክተዋል። ማኅበረሰቡም ታዳሽ ኃይልን በተለይም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን መጠቀም ያለውን አካባቢያዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳን ተረድቶ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
