“ለሚጥል በሽታ መቆጣጠሪያ የሚያገለግለው የፌንቶይን ታብሌት የጥራት ችግር አለበት”

10
ባሕር ዳር: መጋቢት23 /2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሜዲካመን ባዮቴክ ሊሚትድ በተባለ ኩባንያ የተመሠረተ ለሚጥል በሽታ (Epilepsy) መቆጣጠሪያ የሚያገለግለውን የፌንቶይን 100 ሚሊ ግራም (Phenytoin 100 mg) ታብሌት መድኃኒት የጥራት ችግር ስላለበት ከጤና ተቋማት በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ በደብዳቤ ማዘዙን ጋዜጣ ፕላስ አስነብቧል።
የቅርንጫፍ መሥራያ ቤቱ ለሁሉም የጤና ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው በአምራቹ የተመረቱት የዚህ መድኃኒት ባቾች በሙሉ የጥራት ደረጃውን ባለማሟላታቸው ተመላሽ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
ይኹን እንጅ መድኃኒቱን ያልመለሱ ተቋማት ያላቸውን ቀሪ መጠን በደብዳቤ ገልጸው እስከ መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲመልሱ ጥብቅ ማሳሰቢያ ቢሰጥም አንዳንድ የጤና ተቋማት መድኃኒቱን አለመመለሳቸውን አገልግሎቱ አሳውቋል።
ይህንን ትዕዛዝ ተላልፈው መድኃኒቱን ተመላሽ የማያደርጉ ተቋማት ለሚከሰት የጤና መታወክ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በመረጃው በጠቀሰው ባች የተመረተው ምርት ከ19ኙም የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎቶች እንዲሰበሰቡ ነው ያዘዘው።
ዜጎች ለሚጥል በሽታ መድኃኒት ሲጠቀሙ በጤና ባለሙያ የታዘዘላቸው እና ጥራቱ የተረጋገጠ መኾኑን እንዲያረጋግጡ ይመክራል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭቱን ለመቆጣጠር በቴክኖሎጂ የታገዘ የክትትል ሥርዓትን ለመዘርጋት እየተሠራ ነው።
Next articleየኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ከነዳጅ ጥገኝነት የመውጫ መንገድ ነው።