
አዲስ አበባ: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭቱን ለመቆጣጠር ወደ ሥራ ከገባው ግብረ ኀይል በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የታገዘ የክትትል ሥርዓትን ለመዘርጋት እየሠራ መኾኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ የ2018 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈፃጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ አና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡
በወጭ ገቢ ንግድ፣ ከመሠረታዊ ፍጆታ አቅርቦት እና ስርጭት፣ ከገበያ ማረጋጋት፣ ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ከሕገወጥ ንግድ ቁጥጥር አንፃር ባለፉት ስምንት ወራት የተሠሩ ሥራዎችን ነው ያቀረበው።
በሪፖርቱ በወጭ ገቢ ንግድ ከ6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አስታውቋል። የነዳጅ ግብይት ቁጥጥር እና ክትትል ችግር፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር እና የአፈጻጸም ልዩነቶች መኖርን በውስንነት አንስቷል፡፡
ሪፖርቱን መነሻ በማድረግም ቋሚ ኮሚቴው ማኅበረሰቡ ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ የሚገኙ የነዳጅ፣ የመሠረታዊ ፍጆታ አቅርቦት እና ስርጭት ችግሮችን ለመፍታት ምን እየተሠራ እንደኾነ ጠይቋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) በተለይ ከነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ጋር ተያይዞ ያሉ ስጋቶችን ለመቅረፍ የተወሰነውን ልዩ ውሳኔ ወደ ተግባር የማስገባት እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር እና ክትትል ሥርዓትን የመዘርጋት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ቀውስ ጋር በተያያዘ የጊዜያዊ፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎችን ለማምጣት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭትን ለመቆጣጠር ሚኒስቴሩ የወሰነው ልዩ ውሳኔ የሚበረታታ ቢኾንም ውሳኔው መዘግየቱን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል። አዋጁን መሠረት ያደረገ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲዘረጋም አሳስቧል፡፡
ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት እንቅስቃሴ ላይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀናጀ የተጠያቂነት ሥራ እንዲሠራም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝበዋል።
ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የነዳጅ ፍላጎት እና አቅርቦት ለማመጣጠን ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም ይገባልም ብሏል፡፡
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
