
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ከአምባሰል ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ በውጫሌ ከተማ ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ የሰላም እጦቱ እንቅልፍ ነስቶናል ብለዋል። ሰላም ናፍቆናል ያሉት ነዋሪዎቹ ለሰላም ዘብ እንቆማለን ነው ያሉት።
ግጭቱ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። ልማቶች እንዲቀጥሉ ለሰላም ዋጋ መክፈል ያስፈልጋልም ብለዋል።
በወረዳው የተጀመሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እንዲገነባ እና የትምህርት ቤት ግንባታ እንዲስፋፋ ጠይቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ነዋሪዎች ውስጣቸውን በማጥራት እና የሰላም ባለቤት በመኾን ሰላምን ሊያጸኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ሰላም በፍላጎት ብቻ የሚመጣ አይደለም ሰላምን በተግባር ልትገልጡ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዘላቂ ሰላም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና መላው ማኅበረሰብ በጋራ ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
ጎብኝዎች የውጫሌን ታሪክ መጥተው እንዳይጎበኙ እና የአካባቢው ልማት እንዲደናቀፍ ከጠላት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሠራ ያለውን ታጣቂ ኀይል መታገል አለባችሁ ብለዋል። ግጭቱ የትውልድ ስብራትን እየፈጠረ በመኾኑ ሰላምን በማጽናት ማስቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ አስቻይ ኹኔታዎችን እንዲፈጥሩም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጎን በመኾን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሠሩ ነው ብለዋል። ቆም ብሎ በማሰብ እና አካሄድን በመፈተሽ ሰላምን ማጽናት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የመንግሥት የሰላም በር ክፍት መኾኑን አንስተዋል። በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ልትሠሩ ይገባል ብለዋል። የሰላም አማራጭን በማይቀበሉ ታጣቂዎች መንግሥት ጠንካራ ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚያከናውንም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በግጭቱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን አንስተዋል። የንግድ እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል፣ የተማረ የሰው ኀይል እንዳይኖር፣ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዳይሳለጥ አድርጓል ነው ያሉት።
ነዋሪዎቹ የሰላም ባለቤት በመኾን፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት እና ሰላምን በቤት ውስጥ በመገንባት የመፍትሔ አካል መኾን እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ለዘላቂ ሰላም የአዞ እንባ አያስፈልግም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላምን በተግባር ማጽናት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሀቀኛ እና ዕውነተኛ ንግግር በማድረግ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋልም ብለዋል። በመደራጀት አካባቢን መጠበቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ካርድ በማውጣት፣ በመምረጥ እና የምርጫ ጣቢያን በመጠበቅ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲከናወን የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። የተነሱ የልማት ጥያቄዎች ከአካባቢው የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመኾን እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
