ምርጫውን ሰላማዊ፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በጋራ እየሠሩ መኾናቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

8
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እና በሰሜን ጎጃም ዞን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ መክረዋል።
በምክክር መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እና በሰሜን ጎጃም ዞን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችንም በውይይት ለመፍታት በጋራ መሥራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በጋራ እየተነጋገሩ እና እየተወያዩ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) የመጡት አቶ ይሔነው መስፍን አዴኃን መንግሥት በምርጫ የሚመሠረትበትን መንገድ በማሳየት እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አርዓያ በመኾን ለቀጣዩ ትውልድ አሻራ ለማሳረፍ እየሠራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ እንዲኖር ከአጥፊ እና ጠፊ አካሄድ በመውጣት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
አዴኃንም ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከገዥው ፓርቲ እና ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የመጡት ሁናቸው ሳሌ በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚደረግ ምርጫ ሀገርን ያሻግራል ብለዋል። ቀጣዩ ምርጫም በሰላማዊ መልኩ እንዲጠናቀቅ ከፓርቲዎች በተጨማሪ ማኅበረሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በሕዝቡ ተቀባይነት ያለው መንግሥት ለመመስረት ማኅበረሰቡ ከአሉባልታዎች ወጥቶ ካርድ በማውጣት በንቃት መሳተፍ እንደሚኖርበትም ገልጸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በጋራ እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወላጆቻቸውን ያጡ እና ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን ለማሳደግ ተረከበ።
Next article“ሀቀኛ ውይይት በማድረግ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)