
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026 ፎረም፤ ከቻይና፣ ፖላንድ፣ ህንድ፣ ሲንጋፖር እና ኬንያ ከመጡ አጋሮች ጋር የ13 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ታሪካዊ የኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራርሟል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ድረ ገጹ እንዳጋራው በታዳሽ ኃይል፣ በማዕድንና በአረንጓዴ አሞኒያ ዘርፎች ላይ ያተኮሩት እነዚህ ስምምነቶች የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጉልህ ማሳያ ናቸው። የውጭ ምንዛሬ ተመን ሊበራላይዜሽን፣ እና የባንክና ቴሌኮም ዘርፎችን ለንግድ ማኅበረሰቡ ክፍት ማድረግ የመሳሰሉ ቆራጥ እርምጃዎች ግልጽና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠራቸውን በተጨባጭ ያረጋግጣል።
ይህም በዘመናዊ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና በአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አማካኝነት ለዓለም አቀፍ ገበያ ምቹ መዳረሻን ፈጥሯል።
ይህ ዕድገት በሁሉም ስትራቴጂካዊ ዘርፎች በግልጽ እየታየ የሚገኝ ሲሆን፤ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተንተራሰው የሀገራችንን የታዳሽ ኃይል ሀብትን በመጠቀም በሶላር ምርት እና በሃይድሮጅን ፕሮጀክቶች ላይ የተገኘው እመርታ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማዕድን ዘርፍ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራበት ይገኛል።
የኢንዱስትሪ ዕድገታችን አዲስ በሚገነቡት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እየተፋጠነ ሲሆን፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በልህቀት እየተመራ ይገኛል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ትስስር እና በባሕላዊ ቅርሶቻችን የታጀበችው ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ንግድና ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ ኾናለች።
ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ለላቀ አጋርነት እንጋብዛለን፤ ኢትዮጵያ ከነበረው እጅጉን በተሻለ ለንግድ ዝግጁ ናት! ሲልም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መልእክቱን አስተላልፏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
