
ሁመራ፡ መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ግንባታ ተጀምሯል።
ለግንባታው 177 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘለት ተገልጿል። የግንባታው በጀት በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ እና በሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር በጋራ የሚሸፈን ይኾናል።
በግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት አለመኖራቸው ለኑሮ ውድነት መባባስ ምንክያት እንደሚኾኑ ገልጸዋል።
አምራቹ እና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበት የገበያ ማዕከል አለመኖር መሠረታዊ ችግር መኾኑንም አንስተዋል። በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ እና በሰቲት ሁመራ ከተማ የጋራ በጀት ግንባታው የተጀመረው ይህ የገበያ ማዕከል የኑሮ ውድነትን ለማርገብ ፋይዳው የጎላ እንደሚኾንም ጠቁመዋል።
የገበያ ማዕከሉ የኑሮ ወድነትን የሚያቃልል እና የገበያ ትስስርን የሚፈጥር በመኾኑ ግንባታው ወደ ሌሎች ከተሞች እንደሚስፋፋም አመላክተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ፍሰሐ ሀጎስ የገበያ ሥርዓቱን በማዘመን የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ይህ የገበያ ማዕከልም የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ችግር በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።
ገበያ ማዕከሉ አምራቹን ከሸማቹ በቀጥታ በማገናኘት ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም አንስተዋል።
የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ ሀምሳ በመቶው የግንባታው በጀት በከተማ አሥተዳደሩ የሚሸፈን መኾኑን ገልጸዋል።
አካባቢው ብዙ ምርት የሚመረትበት መኾኑን የጠቁሱት ከንቲባው የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያሳድገውም ተናግረዋል። ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
