የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ የወንጀል ተጠያቂነት

6
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1185/2012) ወጥቶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
አዋጁ ሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ኹከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሔርን፤ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሠረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ የሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ዓላማ ያደረገ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መቻቻልን፣ የዜጎች ውይይት እና ምክክርን፣ መከባበር እና መግባባትን ማበረታታት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማጎልበት፤ የጥላቻ ንግግር፣ የሐሰተኛ መረጃ እና የመረጃ ሥርጭት መበራከትን ለመቆጣጠር እና ለመግታት ታስቦ የውጣ እንደኾነም በአዋጁ ተመላክቷል።
አዋጁ ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በሕትመት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሠራጨት የተከለከለ እንደኾነ አስቀምጧል።
ማንኛውም ሰው የሐሰት መረጃን በአደባባይ ስብሰባዎች በብሮድካስት፣ በሕትመት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሠራጨት የተከለከለ ተግባር መኾኑንም አስቀምጧል።
✍️የወንጀል ተጠያቂነት
👉.ማንኛውም ሰው በአዋጁ አንቀጽ አራት መሰረት የተከለከለውን የጥላቻ ንግግር ያደረገ እንደኾነ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ ቀላል እሥራት ወይም ከብር 100 ሺህ ያልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡
👉. በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ እንደኾነ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል።
👉.ማንኛውም ሰው በአዋጅ አንቀጽ አምስት መሠረት ክልከላ የተደረገበትን ተግባር የፈጸመ እንደኾነ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር 50 ሺህ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡
👉. የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከኾነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የሕትመት ውጤት ከኾነ ቅጣቱ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር 100 ሺህ ያልበለጠ መቀጮ ይኾናል፡፡
👉. ሐሰተኛ መረጃ በመሠራጨቱ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ከኾነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደኾነ ከሁለት እስከ ዓምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይኾናል።
👉. በጥላቻ ንግግር ወይም በሐሰተኛ መረጃ ወንጀል መፈጸም ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከኾነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደኾነ እና ጥፋተኛውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምን ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የግዴታ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን ይችላል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የቴሌሳይን መጀመር ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ፍሬሕይወት ታምሩ
Next articleማንነትን መሠረት ያደረገ የሳይበር ጥቃት ሥጋት፦