“የቴሌሳይን መጀመር ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ፍሬሕይወት ታምሩ

6

 

አዲስ አበባ: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ጋር በመተባበር ደኅንነቱ የተጠበቀ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ብሔራዊ የዲጂታል ቴሌሳይን የተሰኘ ሶሉሽን አስጀምሯል።

አገልግሎቱ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን በስፋት ተደራሽ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታው አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሰጠውን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዋና መሥሪያ ቤት እና በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ከ50 በላይ ሚሲዮኖቻችን በከፊል የዲጅታል አገልግሎት ሲሰጡ ቆይቷል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የቴሌሳይን ዲጂታል እና ዲጂታል ሞፋ የተሰኙ ቴክኖሎጂ መር አገልግሎት መጀመሩን ነው የገለጹት።

ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት አገልግሎቱን ለሚሰጠው ተቋማችን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

ለዲያስፖራ አካላት እና መላው ዜጎቻችን ትልቅ የምስራች ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ቴክኖሎጅው የወረቀት ሥራን እና የቢሮክራሲ ሰንሰለትን የሚያስቀር እንደኾነም ዲኤታው ገልጸዋል።

ተቋሙ ብሔራዊ ቅልጥፍናን የማሳደግ እና አገልግሎቱን ከፋይዳ ጋር በማስተሳሰር አስተማማኝ ሥርዓትን የመዘርጋት ሂደት እንደኾነም ተናግረዋል።

ብሔራዊ የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ ተመዝግቦ የሚቀመጥ በመኾኑ ከሙስና የጸዳ እና ግልጽነት የሰፈነበት አገልግሎት መዘርጋት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ “የቴሌሳይን መጀመር በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ብለዋል።

አስተማማኝ የዲጂታል ማንነት ማረጋገጫን፣ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለውን የዲጂታል ፊርማን እና ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የኾኑ የመንግሥት አሠራሮችን አስተዋውቋልም ነው ያሉት።

ይህም ቢሮክራሲን በመቀነስ፤ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ እና ሀገራዊ የዲጂታል ተጠቃሚነትን በማስፈን ረገድ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የትጥቅ ትግል የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ አድቅቆታል” ፍቅሩ ሙሉዬ