
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ እና አካባቢው በትጥቅ ትግል የነበረው ፍቅሩ ሙሉዬ የሰላም አማራጭን ተቀብሏል። የፍቅሩ ሙሉዬ እና የጓደኞቹ የሰላም አማራጭን መቀበል ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።
በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ13ኛ ዕዝ አዛዥ ተስፋዬ አያሌው በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች በሰላም እንዲገቡ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተደረገው የሰላም ጥሪ ፍቅሩ ሙሉዬ እና ጓደኞቹ የሰላም ጥሪውን መቀበላቸውን ገልጸዋል። የፍቅሩ ተከታዮችም እንደሚመጡ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ፍቅሩ እና ጓደኞቹ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋል። ፍቅሩ በሀገር መከላከያ ውስጥ እንደነበርም አስታውሰዋል። የአማራ ሕዝብ ከዚህ በኋላ የጦርነት ቀጣና መኾን የለበትም ያሉት አዛዡ ሰላምን እንፍጠር በሚሉ ምክክሮች ተስማምቶ ሰላምን ፍልጎ በመምጣቱ እንኳን ደህና መጣህ ማለት እፈልጋለሁ ነው ያሉት።
የሰላም አማራጭን የተቀበለው ፍቅሩ ሙሉዬ በታጣቂዎች አደራጃጀት የኮር አዛዥ ኾኖ መቆየቱን ተናግሯል። የአማራ ሕዝብ ተጨቁኗል ብለን ወደ ትግል ሜዳ ወጥተን ነበር ያለው ፍቅሩ በትግሉ ሜዳ ለገንዘብ ጭምር የወጡ ሰዎች እንዳሉ ገልጿል። ወደ ትግል ስወጣ ማንም አስገድዶኝ አይደለም፤ የወጣሁት ትክክለኛ ትግል ያለ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን ትግሉ የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ የሚያደቅቅ እና በድህነት አረንቋ የሚዘፍቅ ነው ብሏል።
ከአማራ ሕዝብ ጠላቶች ጋር አብሮ ወልቃይትን እና ራያን የሚሸጥ ትግል ለአማራ ሕዝብ እንደማይጠቅምም ተናግሯል። ትግሉ ለአማራ ሕዝብ ጠላቶች እንደተሸጠም ገልጿል።
ሌሎች ታጣቂዎችም የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርቧል። የትጥቅ ትግሉ የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ አድቅቆታል ነው ያለው። ትግሉን የሚመሩት ኃይሎች በጥቅም ተቧድነው ለግል ጥቅም እየተጠቀሙበት መኾኑንም ገልጿል።
ትግሉ ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ነገር ግን ከቀበሌ እና ከንዑስ ወረዳ አልወጣም፤ ሁሉም በየጎጡ ነው የሚታገለው ብሏል። ከአሁን ቀደም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ኾኖ ሀገሩን ማገልገሉንም አስታውሷል።
አማራ ተበደለ ሲባል ለትግል ወጥቼ ነበር፤ የበደልነው ግን እኛው ነን፤ ምክንያቱም ትግሉ የገንዘብ መሰብሰቢያ ኾኗል ነው ያለው። ጦርነት ለማንም አይበጅም ያለው ፍቅሩ የእውነት ትግል አለመኖሩንም ገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
