“ሀረር የሰላም ተምሳሌት ከተማ ናት ” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ

5

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስቴር “የሰላም ቱሪዝም ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ለማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በሀረር ከተማ የምክክር እና ጉብኝት መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።

መርሐ ግብሩ በአካባቢው ያሉ የቱሪስት መስህቦች እና ታሪካዊ ሥፍራዎችን በማስጎብኘት የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው።

የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ የቱሪዝም ዘርፉ ኢኮኖሚ እንዲያመነጭ በማስቻል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሰላም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሀረር ከተማ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ባሕል እና ቋንቋ ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት የሰላም ተምሳሌት ከተማ ናት ብለዋል።

በተለይ በተቀራራቢ ርቀት የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አንዱ ለሌላኛው ስጋት ሳይኾኑ ማኅበረሰቡም በሰላም እና አብሮነት ተማምነው የሚኖሩባት ከተማ መኾኗን ገልጸዋል።

ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ያስመዘገበች እና የክልሉን ዕድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ የተለያዩ የቱሩዝም መዳረሻዎችን በጉያዋ አቅፋ የምትገኝ ከተማ መኾኗንም ጠቁመዋል።

ከ500 ዓመታት በፊት ዓለም አቀፉን የጀጎል ግንብ ቅርስ ማኅበረሰቡን አስተባብሮ መገንባት መቻሉ በወቅቱ የነበረውን የዕውቀት ከፍታ የሚያሳይ ነው ብለዋል። በውስጧ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም ሰላም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል።

መርሐ ግብሮችም ቅርሶችን ለማስተዋወቅ እና ለሰላም እሴት ግንባታ አበርክቷቸው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።

ከሀረሪ ክልል ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ቀጣዩን ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ለማስቻል ሰላም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአጣዬ ከተማ ወጣቶች የጸና አቋም ይዘው ለሰላም እየሠሩ ነው።
Next article“የትጥቅ ትግል የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ አድቅቆታል” ፍቅሩ ሙሉዬ